Wednesday, June 22, 2016

የፌደራል ፖሊስ አባላት ኮንሶ ከተማን እንደገና መቆጣጠራቸው ተሰማ

ሰኔ  (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሰኔ 13 ቀን 2008 ዓም ጀምሮ በኮንሶ የሚታየው ውጥረት መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋን ከተቆጣጠሩ በሁዋላ 4 ነዋሪዎችን አፍነው መውሰዳቸው ታውቋል። ይህንን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን፣ ወታደሮቹ በወሰዱት እርምጃ በርካታ ነዋሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የደቡበ አሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ መኮንንም አቶ ሰለሞን ሰንጎ፣ አቶ በርሻ ከጎያ፣ አቶ ኩሴ አይሎና ሌላ አንድ ስማቸው ያልታወቀ ግለሰብ ታፍነው መወሰዳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ አንድ ወጣት በከፍተኛ ሁኔታ መደብደቡንና ፖሊሶች ይዘውት መሄዳቸውን ይሁን እንጅ ያለበትን ሆስፒታል ለማወቅ አለመቻሉን ገልጸዋል።
በከተማው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውንም አቶ አለማየሁ አክለው ተናግረዋል።
የኮንሶ ህዝብ ራሱን ችሎ በዞን ደረጃ እንዲተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ታስረዋል፣ ብዙዎቹም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

No comments:

Post a Comment