Friday, June 17, 2016

በባህርዳር በቀበሌ ቤቶች ዙሪያ አመራሮች ተወዛገቡ

ሰኔ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዋጅ ቁጥር 47/67 ትርፍ ቤትን ለመንግስት ባደረገው አዋጅ የተወረሱ የቀበሌ ቤቶችን አመራሩ ለራሱ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በመኖሪያነትና በንግድ ቤትነት የሚገለገልበት አካሄድ አግባብ አለመሆኑን ሰሞኑን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር አገልግሎት አቅርቦትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፋሲል ሙሉ ተናግረዋል።

“ድሃ ይቅደም!” የሚሉት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር ፣ ህብረተሰቡ በዚህ አሰራር መማረሩን ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ በፍትህ ተከራክሮ ነጻ ያደረጋቸውን ቤቶች አመራሩ “መመሪያነው!” በሚል ቀድሞ ለመያዝ መሞከሩ መሰረታዊ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድሃ ወጥቶ አመራሮች የገቡባቸው ቤቶች መረጃ በእጃቸው እንዳለ የሚናገሩት ሃላፊ በዚህ ጉዳይ በርካታ አቤቱታዎች ለከተማ አስተዳደሩ እንደቀረቡ ተናግረዋል፡፡በከንቲባውም ሆነ በቅሬታ ሰሚው ጉዳያቸውን መፈጸም ያልቻሉ ቅሬታ አቅራቢዎች በየቀኑ ሲያለቅሱ መዋላቸው ያደባባይ ሃቅ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው ፣ የቀበሌ ቤቶች የህዝብና የመንግስት ሃብት እንጅ የአመራሩ ባለመሆኑ ቅድሚያ የሚገባው ህብረተሰቡ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በባህርዳር ከተማ በርካታ ባለሃብቶች የቀበሌ ቤትን ያለአግባብ በመያዝ ቢጠቀሙም፤ ምንም ሃብት ላላፈሩና በከተማዋ ተወልደው ላደጉ ምሩቃን ለማስረከብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች እያደናቀፉባቸው መሆኑን የሰፈነ ሰላም ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ማሩ አላምረው አሳውቀዋል፡፡
በዚህ ከተማ ላይ ሃብት በማፍራት በከፍተኛ ደረጃ ያደጉት ባለሃብቶች የትልልቅ ድርጅት ባለቤትና የበርካታ ንግድ ድርጅት አንቀሳቃሽ ቢሆኑም ላላደገና ምንም ሃብት ለሌለው እንዲለቁ ሲጠየቁ ከፍተኛ ግብግብ በመፍጠር ፍጹም የአልጠግብ ባይነት መስመር በመያዛቸው ክፍለ ከተማው በመመሪያና ደንቡ መሰረት ለመስራት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ባለሃብቶች በተለያዩ መንገዶች በመጓዝና ከበላይ አመራሩ ጋር በመግባባት አሰራሩን በማደናቀፍ ላይ በመሆናቸው ክፍለ ከተማው የማስፈጸም አቅሙን እንዲያጣ ማደረጋቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡ለባህርዳር ከተማ አስተዳደር አገልግሎት አቅርቦትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ጉዳዩን በማስመልከት ደብዳቤ ቢጽፉም የተሰጣቸው ምላሽ “ባለሃብቶቹ ሃብት ቢያፈሩም ባሉበት እንዲቆዩ” የሚያዝዝ ነው በማለት ያላቸውን ቅሬታ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ተጠይቀው የመለሱት የባህርዳር ከተማ አስተዳደር አገልግሎት አቅርቦትና አስተዳደር ጽህፈትቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል ሙሉ ዋናው የዚህ ቅሬታ ምንጭ የክራይ ሰብሳቢነት ምንጭ በመዘጋቱ ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አሰተዳደሩን ሃላፊ ንግግር የተቃወሙት የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ማሩ በተሰጣቸው ምላሽ ተቃውሞ ማቅረባቸውን ተናግረው የተሰጠው ምላሽ የህዝብን ወገናዊነት ያጎደለ መሆኑን አክለዋል፡፡ ግለሰቦቹ ከ30 እና 40 ዓመት በፊት ሃብት ያላፈሩ ቢሆኑም በአሁኑ ሰዓት ግን ከፍተኛ ባለሃብት በመሆናቸው የመንግስትን ቤት በመልቀቅ ስራ አጥ ለሆኑት ወገኖች መገልገያ ሊያስረክቡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡አንድን ድሃ “የመኖሪያ ቤት ተመርተሃል” በሚል የመንግስትን ቤት ስያስለቅቁ በዝምታ የሚመለከተው የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ በነዚህ ባለሃብቶች ላይ ሊወሰድ የነበረውን ርምጃ ማስቆሙ እንዳሳዘናቸው አክለው ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment