Wednesday, June 29, 2016

በሃመር ወረዳ የተጀመረው ግጭት መቀጠሉ ተሰማ

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሃመር እና ኤርቦሬ ጎሳዎች መካከል የተጀመረው ግጭት ተባብሶ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ችግሩ ከግጦሽ መሬት ጋር በተያያዘ ይጀመር እንጅ፣ ከትናንት ጀምሮ መልኩን በመቀየር በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሎአል።
የአገር ሽማግሌዎች ችግሩን ለመፍታት ጥያቄ ሲያቀርቡ የዞኑ የፖለቲካ ምክትል ሃላፊና የሀመር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወሌ ለአገር ሽማግሌዎች_ አርበኞች ግንቦት7 ቶች እዚህ አካባቢ ገብተዋልና ጥንቃቄ አድርጉ በማለት ጉዳዩን ወደ አልሆነ አቅጣጫ በመውሰዳቸው የሽምግልናው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። አስሌ በሚባለው ቀበሌ አካባቢ ግጭቱ መባሳሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ያለፍላጎታቸው ለልማት በሚል ደሞዛቸው የተቆረጠባቸው የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ተቃውሞአቸውን መግለጻቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል። በ ፋብሪካ ቁጥር 1 እና 2 የሚገኙ ሰራተኞች  ለጅንካ ልማት በሚል   ከደርጃ 1-6፣ 500 ብር፣ ከ7-1፣ 800 ብር፣ ከ13-18፣ 1200 ብር፣ ከ 19-26 ደግሞ 1500ብር የተቆረጠባቸው ሲሆን ፣ ሰራተኞች በማኔጅመንቱ ላይ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም ነዋሪዎች በግድ ገንዘብ እንዲከፍሉ መደረጉን እየተቃወሙ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment