Friday, June 17, 2016

19 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መንገድ ላይ ማለቃቸው ተዘገበ

ሰኔ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰሌዳ ቁጥሩ AFB 496 በሆነ የዛንቢያ የአሳና ባቄላ መጫኛ ኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ የነበሩ 19 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እረቡ  ሚውንዳ ድንበር አቅራቢያ ሞተው ተገኙ።

በኮንቴነሩ ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ የተጫኑ 73 ስደተኞች ሲሆኑ ከሟቾቹ በተጨማሪ በሕይወት የተረፉት ላይም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዘግናኝ እልቂት መድረሱን ተከትሎ የዛንቢያ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የሕገወጥ ስደተኞችን ዝው ውር ለመግታት አፋጣኝ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ለስደተኞቹ ሞት መንስዔ የሆነው በተጫኑበት ወቅት የአየር እጥረት በመከሰቱ ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳጡና የሟቾቹ 19 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አስከሬን ወደ ኒዶላ ማእከላዊ ሆስፒታል መወሰዱን ፓሊስ ገልጿል። የ29 ዓመቱ የመኪናው አሽከርካሪ የነበረው ዛንቢያዊያን ኤዲዋርድ ሲምዋባ የ37 ዓመቱ ረዳት አሸከርካሪውን  ኬስታ ካኒያንታን  ጨምሮ 54 ከአደጋው የተረፉ ኢትዮጵያዊያን በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ኒዶላ ተወስደዋል።

ስደተኞቹ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀት እንደረሰባቸውና መጠለያና አልባሳት ወደሚያገኙበት ስፍራ በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም አማካኝነት ወደ ዋና ከተማዋ ሉሳካ የሚያመሩበት ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንም የስደተኞች ጉዳይ ክፍል ገልጿል።  በታንዛኒያ አዋሳኝ ድንበር በሚባላ በኩል ሕገወጥ ስደተኞች በብዛት እንደሚገቡ የአገሪቱ የስደተኞች ጉዳይ አስታውቆ ግብረኃይል በማቋቋም ፍልሰተኞችን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወንጀለኛ ህገወጥ ስደተኞች አዘዋዋሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአገሪቱ የድንበር ፓሊስ አስታውቆ የዛንቢያ ዜጎች ከእንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ስራ እንዲታቀቡ ማሳሰቡን ሉሳካ ታይምስ ዘግቧል። ከአራት ዓመታት በፊትም በተመሳሳይ በኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የነበሩ 43 ኢትዮጵያዊያን ታፍነው መሞታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ቁጥራቸው 58 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ሕንድ ውቂያኖስ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ከተደበቁበት በትናንትናው ምሽት መያዛቸውን የታንዛኒያ ፓሊስን ጠቅሶ ዘሲቲዚን ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment