Monday, April 25, 2016

በድሬዳዋ በርካታ ሰዎች በጎርፍ ተወሰዱ

ሚያዚያ ፲፭(አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሚያዚያ 17 ንጋት ላይ በድሬዳዋ የጣለው ከባድ ዝናብ እስካሁን ድረስ በትንሹ 15 ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ወደ መልካ ጀብዱ የሚወስደው ድልድይ የተሰበረ ሲሆን አንድ ገልባጭ የጪነት መኪናም በጎርፍ ተወስዷል። ወደ መልካ ጀብዱ በሚያሻግረው ወንዝ አንድ ድልድይ ተሰብሮ በህዝብ ማመላለሻ መኪና ውስጥ የነበሩ 18 ሰዎች መወሰዳቸውን እንዲሁም 1 ዩዲ ገልባጭ መኪና ረዳትና ሹፌር በጎርፍ መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ፖሊስ የሟቾቹ ቁጥር 4 መሆኑንና ፍለጋው መቀጠሉን ገልጿል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት በጣሊያን ጊዜ የተሰራው ድልድይ ሊፈርስ የቻለው፣ የጎርፍ መከላከያ በሚል የተሰራው ተፋሰስ ጠቦ በመሰራቱ ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል በምስራቅ ኢትዮጵያ አፋጣኝ እርዳታ በወቅቱ ካልቀረበ የሞት አደጋ ማንዣበቡን አንድ የኖርዌይ ድርጅት ገለጸ።
በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለመታደግ በሚደረገው የነፍስ አድን ስራ ላይ ወቅቱን ሳይጠብቅ የሚጥለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች እርዳታ ለማዳረስ ተጨማሪ እክል መሆኑን ረዩተርስ የኖርዌይ የስደተኞች ድርጅትን በመጥቀስ ዘግቧል።
የበልግ ዝናቡ ባስከተለው ጎርፋ ሳቢያ በምስራቅ ኢትዮጵያ በአፋርና ሶማሊያ ነዋሪዎች በጎርፍ አደጋው በድርቁ የተጠቁና የደከሙ የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
የጎርፍ አደጋው በቤት እንስሳት ላይ ብቻ ሳይሆን በነዋሪዎች ላይም አደጋ ማድረሱን ድርጅቱ አስታውቆ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ካልቀረበ ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች መኖራቸው አያጠራጥርም ብሎአል። በሶማሊያ ክልል በጅጅጋ ከተማ የክልሉ ባለስልጣናትን መረጃ በመንተራስ ከሃያ ስምንት ሰዎች በላይ በጎርፍ ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና ጎርፉን ተከትሎ ተላላፊ የኮሌራ በሽታ መከሰቱም ተዘግቧል።
ከአስሩ ስምንቱ አርሶ አደር የሆነባት ኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት ሳቢያ ለአደገኛ ርሃብ መጋለጧን ድርጅቱ ጠቁሞ፣ አፋጣኝ እርዳታ በማቅረብ የነዋሪዎችን ሕይወት መታደግ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማሳሰቡን ሮይተር ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment