Sunday, April 3, 2016

ያደባባይ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ | ፈቃደ ሸዋቀና

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ:
ስለምልካም አስተዳደር ችግር ካንዴም ሁለቴ አምረው ሲናገሩ ሰምቼዎት የሚናገሩት እንደተለመደው ላልኩ ባይነት ያህል ነው ወይስ ቆርጠው ሊዋጉት ተነስተዋል የሚል መንታ ሀሳብ ላይ ቆሜ በተግባር የሚያደርጉትን ከሚጠብቁ የዚች አገር ልጆች እንዱ ነኝ። የተናገሩትን የሚመስል እንድ ርምጃ ወስደው አስካይዎት ድረስ ያፍዎን የልብዎ ከዚያም የተግባርዎ እንዲያደርገው እጸልያለሁ። የተናገሩትን ወደ ሥራ ለማዞር ያለዎትን አቅም ብጠራጠርም ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም እንደሚባለው ከልብዎ አስበው ከተነሱ ቢያንስ ባደባባይ እንዳላየ እያየን “መቼስ ምን ይደረግ” እያልን የምናልፋቸውን የተወሰኑትንና በቀጥታ የሚመለከቱዎትን ብልሹ ያስተዳደር ጥፋቶች በግልዎም ጥረት ቢሆን ማቆም አያቅትዎትም። ዞሮ ዞሮ ለሚደርሰው ጥፋትና ያስተዳደር ብልሹነት ሁሉ የአገሪቱ አስተዳደር አናት ላይ እንደመቀመጥዎ ለችግሩ የመጀመሪያው ተጠያቂ ርስዎ ነዎት። ዛሬ እኛ አቅም አጥተን ተጠያቂ አድርገን ባንፋረድዎትም ታሪክ ሲያብጠለጥልዎት ይኖራል። ስለዚህ ለመተማመኛም እንዲሆን ህዝብም ይህ ነገር የምር ነው እንዲል ለምሳሌ የሚሆን ርምጃ ባንድ የተበላሸ የመንግስት አሰራር ላይ ወስደው ያሳዩን።

መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ብልሹ አስተዳደር እንዲወገድ ጥናት ያደረገው ግብረ ኃላችሁ ሪፖርቱን ባቀረበበት መድረክ ላይ በቪዲዮ እንዳየነው በጅጉ ጎልቶ የተሰማው የርሶ ድምጽ ነበር። ብዙ ተስፋ የቆረጡ ወገኖች የፐብሊክ ሬሊሽንስ ስራ ነው ብለው ቢያጣጥሉትም እኔ እስቲ ቀጥሎ የሚያደርጉትን እንይ በማለት ለመጠበቅ ከመረጡት ውስጥ ነኝ። በኔ አስተሳሰብ ያገራችን የመልካም አስተዳደር ችግርም መፍትሔውም ብዙ ጥናት የሚሻ ነገር አልመሰለኝም። ነገሩ ሮኬት ሳይንስ አይደለም። ብዙው የመልካም አስተዳደር ችግር ደግሞ እናንተ ባለስልጣኖቹ መሀል ላይ ቆማችሁ የምታዩት ነው። በቀደም ሀገሪቱ ውስጥ ግለሰቦች እስር ቤት አላቸው ብለው የነገሩንና ያስደመሙን ርስዎ አይደሉ?
እኔ ከሀገሮች ልምድ አገላብጬ ያገኘሁትን ዝባዝንኬ የሌለበት የመልካም አስተዳደር ማስፈኛ ትልቁን ዘዴ ልንገርዎት። የመልካም አስተዳደር መስፈን አለመስፈን ጉዳይ ከህዝብ ተሳትፎ ጋር የተያያዘ ነው። ያስተዳደር ችግር ሙስናና የስልጣን ብልግና እንዲወገድ ከተፈለገ በመንግስት ጥረት ላይ ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ይጠይቃል። መልካም አስተዳደር የሚመኝ ባለስልጣን የመጀመሪያ ስራ ይህንን የህዝብ ተሳትፎ መኮትኮትና ማሳደግ ነው። የግልጽነት (Transparency) ባሕል የሚዳብረው ከዚህ ጀምሮ ነው። የህዝብ ተሳትፎ ሲባል በእምነት ላይ የተመሰረተና ጥርጣሬ የሌለበት በሀገር መሪዎች አርአያነት የታገዘ ተሳትፎ ማለት ነው። ሕዝቡ በመንግስት ላይ እምነት ከሌለው ከልቡ ለመሳተፍ ይቸገራል። ባጭሩ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ቁልፉ በእምነት ላይ የተመሰረተ የህዝብ ተሳትፎ ነው። ሌላ ብዙ ዝባዝንኬ የለውም። ሕዝቡ መንግስትንና የበላይ መሪዎችን ሲያምንና ተቆርቋሪነታቸው ከልብ የመነጨ ነው ብሎ ካረጋገጠ በህዝብ ላይ የሚባልግ የመንግስት ሹም አይኖርም። ችግሩን አጋልጬ ያገባኛል ብዬ ተጋፍጬ በኋላ ለጥቃት ብጋለጥ የሚደርስልኝ አይኖርም የሚል ዜጋ በበዛበት ሀገር መንግስት የሙሰኞች መፈንጫ ሆኖ ነው የሚቀረው።
እዚህ የምኖርበት የስደት ሀገሬ አገልግሎት ለማግኘት የመንግስትም ይሁን የግል ድርጅት ውስጥ ሄጄ አንዱ ትንሽ ቢያጉላላኝ ራሱን አለቃህን ጥራ ብዬ አፋጥጬ በደሌን ላለቃው ነግሬ ሁለተኛ
እንዳይለምደው አድረጌው የምፈልገው አገልግሎት ተቀላጥፎልኝ ነው የምሔደው። ይህን የማደርገው የኔን መጉላላት የማይቀበል ስርዓት ባገሩ ላይ መስፈኑን ርግጠኛ ስለሆንኩ ነው። እንዲህ አይነት ነገር እያሳደዱ የሚያጋልጡ ጋዜጠኞች ደግሞ ከቀበሌ አስከሀገር ደረጃ አሉ። እናንተ ባንድ በኩል ጋዜጠኛ እያስፈራራችሁና እያሰራችሁ በሌለ በኩል ስለ ማልካም አስተዳደር ስታወሩ ከልባችሁ መሆኑን እንጠረጥራለን። እቅጩን ልንገርዎት። ትችትና ነጻ የህዝብ አስተያየት እንደጦር የሚፈራ መንግስት መልከ-ጥፉ እንጂ መልካም አስተዳደር ማሰፈን አይችልም። የዚህ አይነት መንግስት ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ራሱንም ከውድቀት አያድንም። አሁን ኦሮሚያ ፣ ጎንዳርና ኮንሶ አካባቢ ከሕዝብ ጋር ጦርነት የገጠማችሁትና ከድጥ ወደማጥ እየገባችሁ ያላችሁት በጊዜ መስማት የነበረባችሁን ነገር ንቃችሁ በመተዋችሁ ይመስለኛል። አሁን የያዛችሁት ግደለው ፣ በለው ፣ እሰረው አካሄድ ለማንም እንደማይበጅ የሚነገራችሁን ምክር ብትሰሙ ከብዙ ጥፋት መዳንም ችግሩን መቋቋምም ትችሉ ነበር።
የህዝብ ተሳትፎ እንዴት ይጎለብታል ከይትስ ይጀመራል ብለው ይጠይቁኝ ይሆናል። ህግና አዋጅ በማውጣት መስሎዎት ከሆነ ተሳስተዋል። ይህ ዝም ብሎ ድሪቶ የማብዛት ጉዳይ ነው። ባለስልጣኖቹ እንደፈለጋችሁ የምትጥሱት ጥሩ ህግ ወረቀት ላይ ሞልቷችኋል። ህዝብ ከልቡ እንዲሳተፍ ባለስልጣኖች አርአያነት ያለው ስራ ሲሰሩ ማየት ይፈልጋል። ይመኑኝ ቢያንስ እርስዎ በግልዎ ሊለውጧቸው የሚችሉ ነገሮችን ሲለውጡ ካየ ህዝቡ ተሳትፎው ይጨምራል። ትንሽ መንገድ የመቅደድ ጉዳይ ነው።
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር
እኔ በዚህ ደብዳቤ ላይ ስለዘርፈ ብዙው የሀገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር ብዙ ለመዘብዘብ አይደለም አነሳሴ። የዚህ ደብዳቤዬ አላማ እርሶ በግል ስልጣንዎ ሊሰሩ ከሚችሏቸው ነገሮች እንዱንና ሁላችንንም ወደተራ እንስሳነት ያወረደ የመንግስትዎን አንድ የተበላሸ መልከ ጥፉ ያስተዳደር ስራ እንዲያስቆሙ ለመጠየቅ ነው። ይህን ካስቆሙ ከላይ ያነሳሁትን የአርአያነት ጥያቄ እንደጀመሩት ሊወስዱት ይችላሉ። ችግሩን ወደ መፍቻው አቅጣጫም ብዙ ማይል እንደሄዱ እቆጥረዋለሁ። ከላይ ያነሳሁትን የህዝብ አመኔታ ችግር ሙሉ ለሙሉ ባይፈታውም ይቀንስልዎታል። ሌላውንም ችግር ለመፍታት መንደርደሪያ ይሆንዎታል። በሕዝብ የሚከበሩና የሚወደዱ ሰውም ያደርግዎታል።
ህዝብና የታሪክ ፍርድ ባይፈሩ እንኩዋን እባክዎ ስለፈጠረዎ አምላክ ብለው እስረኛ ማሰቃየት (ቶርቸር) የሚባል የምርመራ ዘዴ ያስቁሙ። ሌላውን ግድያውን ፣ ማስፈራራቱን ፣ ማንገላታቱን ፣ አፈናውንና ብዙውን የመብት ጥሰትና ይፈትሕ መጓደል ያስቁሙ እያልኩዎት አይደለም። እንድ ግለሰብ በጃችሁ ላይ ከወደቀና ካሰራችሁት በኋላ በአካሉና በሕሊናው ላይ የምጥፈጽሙትን ተሰቃዩንም ራሳችሁንም ከሰብዓዊ ፍጡር ውጭ የምታደርጉበትን ሰቆቃ (ቶርቸር) ብቻ ነው የምለው። ቶርቸር በአለማቀፍ ሕግም ይሁን በእኛ ሀገር ሕጎች የተከለከለና የሚያሰቃየውን ሰውም ሆነ የሚሰቃየውን ሰው ከስብዕና ውጭ የሚያደርግ እንስሳዊ የችግር መፍቻ ዘዴ ነው። በሰለጠነው አለም ሰው ቀርቶ እንስሳት ማሰቃየት በጅጉ የተከለከለ ነው። ይህን ነውር በስፋት እያከናወኑ ስለሀገር ሕዳሴና ስለመልካም አስተዳደር ማውራት በውነቱ ፍጽም ከንቱ ግብዝነት ነው። ግፍና ሰቆቃ እንዲካሄድ በሚፈቅድ መንግስትና አገር ውስጥ ጥገና እንኩዋን ቢደረግ የሚገኝ አስተዳደር መልካም ሳይሆን መልከ ጥፉ ብቻ ነው።
በዘመናችን ሰው ከማሰቃየት የተሻሉ ብዙ የምርመራ ዘዴዎች መኖራቸውን ባለሙያዎቹ ሲናገሩ እንሰማለን። እንደሚቻልም በመረጃ ያሳዩ ብዙ ናቸው። የምኖረው ሁሉን ነገር አፍረጥርጦ ለመወያያት ገደብ የሌለበት ሀገር ነው። በዚህ የቶርቸር ጉዳይ ላይ የሚወያዩ የምርመራ ባለሞያዎች በቶርቸር የሚገኝ መረጃ አዛላቂ ጥቅም እንደሌለው እንዴውም በጣም አሳሳችና ከሰህተት ወደ ስህተት የሚወስድ ግኝት ላይ እንደሚያደርስ ብዙ ሲናገሩ እንሰማለን።
ይህን የሰቆቃ ስራ የሚሰሩት ሰዎች አንዳንድ ጊዜ እንደግል መዝናኛቸው ሊያደርጉት ወይም ግላዊና ቡድናዊ የጥላቻ ስሜታቸውን የሚያረኩበት ሊያደርጉትም እንደሚችሉ ማሰብ ይጠቅማል። በየማህበረሰቡ ውስጥ የስቃይ ደስተኞች (Sadists) መኖራቸውን ሊያውቁ ይገባል። አሁን ከሰለባዎቹ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው አዲስ አበባ አራዳ የሚገኘው ማዕከላዊ ምርመራ መስሪያ ቤት በዚህ አይነት ሰዎች የተወረረ ነው የሚመስለው። ምናልባትም ሰዎች በጭካኔ መደሰት (sadism) የሚማሩበት ቦታ ወደመሆን ሳይዞር አልቀረም። የዚህን ምልክት ተሰቃይተው የወጡ ዜጎች ደረሰብን የሚሉት ድብደባ አዋራጅ ስድብና ዘለፋ ላይ ይታያል። የብሔረሰቤን ስም እየጠሩና እያዋረዱ ገረፉኝ እያሉ ሲናገሩ የሰማናቸው ሰዎች ቁጥር ብዙ ነው። ሁሉም ተሰቃዮች ሲወጡ ሲናገሩ እንደምንሰማው የሰቆቃው መስሪያ ቤት ሰራተኞች ካንድ ብሔረሰብ የመጡ ስዎች ናቸው ይላሉ። ይህ ሙያዊ ምርመራ ሳይሆን በመላው ታክስ ከፋይ በሚተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ቡድናዊ ፍላጎትን ለመጠበቅ የሚደረግ የብልሹ አስተዳደር ምልክት ነው። ጭካኔውንም የሚያበዛው ይህ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም። ባልተወለደ እጅ የሚፈጸም ጭካኔ መሆኑ ነው። በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ እንደሰፈነው ስርዓት ያለ የብልሹ አስተዳደር ምሳሌ ሀገራችን ውስጥ መስጠትም ይከብዳል። ክቡርነትዎ ስለመልካም አስተዳደር ሲያሰሙ የሰማንዎት ምሬት ይህን የሚጨምር ካልሆነ ፈጽሞ ዋጋ የለውም።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር
እባክዎን በመጀመሪያ ይህን ያድርጉ። መሃል ከተማችን ላይ እንደጌጥ የቆመውን አራዳ ጊዮርጊስ በላይ ያለውን ይህን ማዕከላዊ የሚባለውን የሰቆቃ ማዕከል ይዝጉት። ከሳምንታት በፊት “ገራፊዬን አየሁት” በሚል ርዕስ አንዱ ሰቆቃ የተፈጸመበትና መጨረሻ ላይ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሊመጣ ሲል በነጻ የለቀቃችሁት ወጣት ጦማሪ የጻፈውን አጥንት ድረስ ገብቶ የሚሰማ ጽሑፍ ያንቡት። እውነቱ ነው። ሰው እንዴት መሀል ከተማ ላይ ያን የመሰለ ሁላችንንም የሚያዋርድ የሰቆቃ ማዕከል ይዞ ከራሱ ጋር የታረቀ ፣ የተከበረ ህዝብና ዜጋ መሆን ይችላል? የዚህን አይነት መንግስትና ሹማምንቱን እንፈራቸው እንደሆነ እንጂ እንዴት ልናከብራቸው እንችላለን? ይህን በዋና ከተማችን መሀል አራዳ ላይ አስቀምጠን ምን አይነት የዜግነት ክብር ነው ሊሰማን የሚችለው? የሰው ልጅ ሰውነት በኤሌክትሪክ ገመድ አየተቀረደደ ፣ ወንዶች ብልታቸው ላይ ውሃ የሞላ ጠርሙስ እየሞሉ እያንጠለጠሉ ፣ ሴት ልጆችን ርቁታቸውን መርማሪዎች ፊት እንዲቆሙና ውርደት እንዲሰማቸው ማድረግን የመሰለ ግፍና ሰቆቃ የሚካሄድበት ሀገር መሪ መሆን የሚያዋርደው እርሶንና ባካባቢዎ ያሉ ባለስልጣኖችን ሁሉ ነው። ስለዚህ ነገር በተወራ ቁጥር ሹማምንቱ አውሬ እንጂ ሰው እኮ መስላችሁ አትታዩንም። በቅርቡ እንዱ ሰለባችሁ መርማሪዎቼ ሱሬዬን አስወልቀው እላዬ ላይ ሽንታቸውን ሸኑብኝ በማለት እያማረረ ሜዲያ ላይ ሲናገር እየዘገነነኝ ሰማሁት። ይህ መቼም ለምርመራ ሳይሆን ሰው በማዋርድና በማሰቃየት ደስታ ለማግኘት የሚደረግ የሳዲስቶች ስራ ነው። የተገረፈ አካልና የስረኞችን ጩኸት አየሰሙ እንዳላየ የሚያዩ ወይም ሰለባዎቹን ራሳቸውን ማስረጃ እምጡ የሚሉ ዳኞች ይዞስ ስለመልካም አስተዳደር ማውራት እንዴት ይቻላል? የስረኛ አቤቱታ የማይሰማ ዳኛ ባለበት ሀገር ምን አይነት ዳኝነት ነው የሚኖረው? ይህን ጉድ እያስተናገዳችሁ መልካም አስተዳደር ስታወሩ ማን ከልባችሁ ነው ብሎ የከተላችኋል? ይህ ሁሉ ግፍ ጭራሽ አይሠራም ብላችሁ ትክዱ ይሆናል። የመረጃው ብዛት በክህደት ሊስተባበል ከሚችልበት በላይ ሄዷል። ይህ ግፍ በተደጋጋሚ ከብዙ ሰለባዎች ዘንድ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እየተሰማ ነው። የመልካም አስተዳደር መበላሸት ቁንጮ ከዚህ የበለጠስ ምን አለ? ማዕከላዊ የሚባለው ትልቁ የሰቆቃ ተቋም ከቢሮዎ 5 ኪሎሜትር በመይሞላ ርቀት ላይ መሆኑን አይርሱ። አድዋ ድረስ ክብራችንን ለማስመለስ ስንዘምት አብሮን የዘመተው ታቦት አራዳ ጊዮርጊስ አጠገብ ይህን ማዕከል አስቀምጦ ስለምን አይነት ተሀድሶና ሀገር ግንባታ ነው ማውራት የሚቻለው?
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር
ይህን የግፍ ማእከል መዝጋት ቀላል ላይሆን ይችላል። ካንዳንዶች የስራ ባልደርቦችዎ መጠነኛ ፈተና ሊኖርብዎት እንደሚችል መገመት ይቻላል። መዶሻ አዘውትሮ እንደሚይዝ አናጢ ሁሉም ነገር ምስማር መስሎ የሚታያቸው ሰዎች ዞሪያዎ እንዳሉ እናውቃለን። መንግስትና ሕዝብን የሚያጋጭ ችግር መፍታት ሲባል የሚታያቸው ጥይትና ዱላ ብቻ የሆነ ሰዎች በብዛት እንዳሉ ለማረጋገጥ ባለፈው አራት ወር ሙሉ ኦሮሚያ ውስጥ ህጻን አዋቂ ሳይለዩ ሰው የሚፈጁና የሚያስፈጁ ሹሞችዎን ማይት ብቻ ይበቃል። ድርጊታቸው ተቃውሞውንና ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን የበለጠ የሚያባብስ መሆኑን ፈጽሞ ሊገምቱ እንኳን አልቻሉም።
ይህን በየስር ቤቱ የሚደረግ ሰቆቃ ለማስቆም ከልብዎ ከሞከሩ የሚያቅትዎት አይመስለኝም። ከሁሉም በፊት ግን ይህን መሀል ከተማ ላይ የተቀመጠ የውርደት ማዕከል ሊዘጉት ይችላሉ። በዚህ ሳቢያ ሥራዎን ቢያጡም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ውለታ እንደሰሩ ሰው ተቆጥረው በህይወትም በታሪክም በኩራት ይኖራሉ። ብዙ ሚሊዮኖች አክባሪዎም ረዳትዎም እንሆናለን። ይህን ቦታ ይዝጉት። ከዚያ በይስርቻው ያሉትን ማሰቃያዎች መዝጋት የጊዜ ጉዳይ ይሆናል። እባክዎት ይህን ማዕከላዊ የሚባል የሰቆቃ ሰገነት ይዝጉት። ሞክረው ቢያቅትዎት እንኳን ሰቆቃን ለማስቆም የሞከረ አንድ መሪ ነበረ እየተባለ ይነገርልዎታል። ይህ የሰቆቃ ሰገንት በሰውም ብእግዚአብሔርም በሰለጠነው አለም ፊትም እንገት የሚያስዳፋ አሳፋሪ የመልከ ጥፉ አስተዳደር ምልክት ነው። እንገት መድፋት ያለብን ሰለባዎቹና ታዛቢዎቹ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን እናንተም ይህን ሰቆቃ የምትፈጽሙት ሹማምንት መሆናችሁን አይዘንጉ። ይህንን የምድር ላይ ሲኦል ይዝጉት። ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆኑ ደግሞ እባክዎን ኢትዮጵያና ሕዳሴ የሚሉትን ቃላት ባንድ አረፍተ ነገር ውስጥ መጠቀም ያቁሙ።

No comments:

Post a Comment