Wednesday, April 6, 2016

በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት 200 ሺ ብር ድጋፍ አደረጉ

ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)

ኢሳት በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለይም በሃገር ውስጥ ላሉ ዜጎች እያደረገ ያለውን አስተዋጽዖ ለመደገፍ፣ በሃገር ቤት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የ200 ሺ ብር ድጋፍ አደረጉ፣ አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ ኢሳትን ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በሚያዚያ ወር 2002 ዓም የተመሰረተውና ለ6 አመታት በሃገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃ በመስጠት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት በተለያዩ ወቅቶች በሃገር ቤት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአንድ መቶ የኢትዮጵያ ብር ጀምሮ ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የግል ሳተላይት ቴሌቪዥን የሆነ ኢሳት ለመደገፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ አንድ ክልል ውስጥ የ200 ሺህ ብር ድጋፉን የላኩት ወገኖች ኢሳት ተስፋቸውና ብርሃናቸው ጭምር በመሆኑ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በሃገር ቤት የሚገኙና ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ ሌሎች ወገኖችም በውጭ ሃገር በሚኖሩ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ወዳጆቻቸው አማካኝነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ከኢሳት የፋይናንስ ክፍል መረዳት ተችሏል።
በቤተሰብና በዘመዶቻቸው ስም ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖች በኦንላይን ክፍያውን መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፣ በቀጥታ ከባንክ አካውንታቸው ገንዘቡ እንዲወጣ ካልፈለጉም የቪዛና ማስተር ጊፍት ካርድ በመግዛት በኦንላይን ክፍያ መፈጸም እንደሚችሉም የኢሳት የፋይናንስ ክፍል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ባለፉት 6 አመታት በሳተላይት አማካኝነት የሚሰጠውን አገልግሎት ለማወክ በተደረገበት ርብርብ ከ20 በላይ ሳተላይት ለመቀየር ለተጨማሪ ወጪ ቢደረግም አሁን አገልግሎቱን ቀጥሏል።

No comments:

Post a Comment