Thursday, April 7, 2016

የቤት ለቤት ፍተሻ የመርካቶ ነጋዴዎችን አበሳጭቶአል

መጋቢት ፳፱( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በፖሊስ ሀይል እየታገዘ መደብሮቻችንን መፈተሽ መጀመሩ ህገወጥ እርምጃ ነው በሚል የመርካቶ ነጋዴዎችተቃውመዋል።

አንዳንድ ነጋዴዎች ለአዲስ አበባው ሪፖርተራችን እንደነገሩት ፖሊሶች በድንገት ሱቆቻችንን በመውረር ፍተሻ እናደርጋለን በሚል ለእያንዳንዱ እቃ በህጋዊ መንገድ የገባበትን ማስረጃ ካላቀረባችሁ ብለው እንደሚያዋክቡ፣
አንዳንዶች ማስረጃዎችን እስከሚያሰባስቡ እድል እንኩዋን ሳይሰጡዋቸው እቃዎቻቸውን ኮንትሮባንድ ናቸው በሚል ጭነው እየወሰዱ መሆኑ አሳዛኝ ነው ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።
ነጋዴዎቹ አያይዘውም በተለይ ሞባይሎች፣ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መንግስት በላካቸው ሀይሎች እየተዘረፉ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ በበኩሉ ኮንትሮባድን ለመቆጣጠር በመርካቶ አካባቢ በተመረጡ 7 ሱቆች ላይ ሰሞኑን ድንገተኛ ፍተሻ በማካሄድ ግምታቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ የኤሌክትሮኒክስ የኮንትሮባንድ እቃዎች ይዣለሁ ብሎአል።
ባለፉት ወራት በተመሳሳይ ሁኔታ በ29 ሱቆች ላይ እርምጃ መውሰዱንና በድርጊቱ የተጠረጠሩ ነጋዴዎችን እንደሚከስ አስታውቆአል። በዚህ ምክንያት በመርካቶ በተለይ አንዋር መስጊድ አካባቢ በርካታ ሱቆች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ለመገንዘብ ተችሎአል።

No comments:

Post a Comment