Friday, April 22, 2016

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት እነ አቶ አለማየሁ መኮንን በዋስ እንዲፈቱ ተወሰነ

ሚያዚያ ፲፬(አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው መጋቢት 17/08 ተይዘው እስከ ትናንት በሃዋሳ ታስረው የነበሩት የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞን ጽ/ቤት ኃላፊ መምህር ዓለማዬሁ መኮንን፣ የኦህዲኅ አባል የሆኑት አቶ አብረሃም ብዙነህና የቀድሞው አንድነት የዞኑ አስተባባሪ የነበሩት አቶ ስለሺ ጌታቸው ሚያዚያ 13-08-08 ዓም ፍርድ ቤት ቀርበው ምንም አይነት ማስረጃም ሆነ መረጃ ያልቀረበባቸው በመሆኑ ፣ ፍርድ ቤቱ በአስር ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ እንዲፈቱ እንደወሰነላቸው ተከሳሾች ባልቀረቡበት ሁኔታ ተነግሯቸዋል።

ኢሳት የእነ አቶ ኣለማዬሁን እስር በሚመለከት ከዚህ በፊት የዞኑና ከተማው ነዋሪዎች ጉዳዩ በዞኑ የህወኃት አባላትና ተጠቃሚ-ደጋፊዎች ከፈጸሙት የመሬት ቅርምትና በዞኑ ከሚፈጸመው ሙስና ጋር የተያያዘ መሆኑን ይህንን ታሳሪዎች በማጋለጣቸው መሆኑን መግለጻቸውን መዘገቡ ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሚያዚያ 6/08 ከዞኑ ዋና ከተማ ጂንካ በ17 ኪ/ሜትር ርቀት በምትገኘው የደቡብ አሪ ዋና ከተማ በሆነቺው ጋዘር ከተማ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው ጎርፍ አንድ የ17 ኣመት ልጃገረድ ተወስዳ ህይወቷ ማለፉንና፣ በእለቱ የዋለውን ገበያ ተከትሎ ሸቀጦች በጎርፍ በመወሰዳቸው ከፍተኛ ንብረት መወደሙን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የከተማው ነዋሪዎች ‹‹ የተፈጠረው አደጋ መነሻ የከተማው አስተዳደር ከከተማው መቆርቆር ጀምሮ የነበረውን ‹‹የሃሙስ ገበያ ››በመባል የሚታወቀውን ማዕከላዊ የገበያ ቦታ ለመሸጥ ሲል የገበያውን ቦታ ወደ አስቸጋሪ ፣ ለአቅመ ደካማ የማይደረስና ለጎርፍ የተጋለጠ ረባዳ ቦታ ላይ በመቀየሩ እንደሆነና ይህን የከተማውን አስተዳደር ድርጊት የከተማው ነዋሪዎች ቦታው ከመቀየሩ በፊትና በኋላ በየጊዜው፣ በተለያዩ መድረኮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተቃወሙት በማንአለብኝነት የተፈጸመ ተግባር ውጤት ነው፡፡›› ይላሉ።
“አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ እየጠነከረ የሚመጣውን የዝናብ ወቅት ተከትሎ ከዚህ የከፋ አደጋ ሊከተል ይቻላል” በማለት ነዋሪዎች በማስጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment