Tuesday, April 19, 2016

በሃረሪ ክልል ሃብሊና ኦህዴድ እየተወዛገቡ ነው

የክልሉ የኢሳት ወኪል እንደገለጸው፣በሃረር ከተማ የሸንኮር ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አፈንዲ ሰሎሞን በጸረ -ሙስና ኮሚሽን አማካኝነት በከፍተኛ ሙስና ተወንጅልው እስር ቤት መግባታቸውን ተከትሎ፣ የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ( ሃብሊ) እና የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲ ድርጅት ( ኦህዴድ) እየተወዛገቡ ነው። 
አቶ አፈንዲ የሃብሊ አባል ሲሆኑ፣ ኦህዴዶች ሆን ብለውአስገምግመው እንዲታሰር አስደርገውታል በማለት ሃብሊዎች የኦህዴድ መሪዎችን እየወነጀሉ ነው። ክልሉን በዋነኘነት የሚያስተዳድሩት ሃብሊዎች ቢሆኑም፣ ከእነሱ በመቀጠል በሁለተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙት ኦህዴዶች የሃብሊን ስልጣን አይቀበሉትም። ኦህዴዶች ሆን ብለው በሙስና ስም የሃብሊ አባላትን ከጭዋታ ውጭ እያደረጉዋቸው ነው በማለት ሃብሊዎች ቅሬታ ያሰማሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ የሃረር ከተማ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ ያሲን ሁሴን፣ ቀድሞ የቀበሌ ቤት፣ በሁዋላ ደግሞ ጤና ጣቢያ የሆነውን ቤት በማስለቀቅ የግል መኖሪያ ቤት ማድረጋቸውን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞውን ቢገልጽም የሚሰማው ማጣቱን ወኪላችን ገልጾአል። ግለሰቡ ለቤት ማደሻ በሚል 1 ሚሊዮን ብር እንደተመደበላቸው የገለጸው ወኪላችን፣ ለህዝቡ የተዘጋጀው ተለዋጭ ጤና ጣቢያ ለትራንስፖርት አገልግሎት አመቺ አለመሆኑን ጠቅሷል።

No comments:

Post a Comment