Wednesday, April 6, 2016

በጋምቤላ የእርሻ መሬት የወሰዱ 93 ባለሃብቶች መሬታቸውን እንዲመልሱ ተደረገ

ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)

በጋምቤላ ክልል የወረዳ አስተዳደሮች በህገወጥ መንገድ የእርሻ መሬት ተሰጥቷችኋል የተባሉ 93 ባለሃብቶች መሬታቸውን እንደመልሱ ተደረገ።
በህጋዊ መንገድ የእርሻ መሬቱን እደተረከቡ የሚገልጹት ባለሃብቶች በበኩላቸው መሬቱን ከክልሉ ባለስልጣናት በህጋዊ መንገድ ከተረከቡ በኋላ የፌዴራል ባለስልጣናት ርክክቡ ህገወጥ ነው ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

በጋምቤላና ሌሎች ክልሎች ለውጭና ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሲሰጥ የቆየው ሰፋፊ የእርሻ መሬት በመንግስት ላይ ኪሳራን አስከትሏል መባሉን ተከትሎ የመሬት መስጠቱ ሂደት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።
መንግስት ደርሶበታል የተባለን ኪሳራ እንዲያጣራ የተቋቋመ አካልም በክልሉ ባለሃብቶች ያለግባብ ተሰጥቷል የተባለ 200ሺ ሄክታር መሬት እንዲመለስ ማድረጉን የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ማክሰኞ ገልጿል።
ይኸው ሰፋፊ የእርሻ መሬትም በ93 ባለሃብቶች ተይዞ የነበረ እንደሆነ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዳንዔል ዘነበ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
መሬቱን በህጋዊ መንገድ ከክልሉ እንደተረከቡ የሚገልጹት ባለሃብቶች በበኩላቸው በፌዴራልና የክልል መንግስታት በኩል የመናበብ ችግር በመኖሩ ሳቢያ በስራቸው ላይ ኪሳራ መድረሱን እንዳስታወቁ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ በጎግና ዲማ ወረዳዎች ለ93ቱ ባለሃብቶች የተሰጠው መሬት ለኢኮኖሚ ዞን የተያዘ እንደነበርና ባለስልጣናት በህገወጥ መንገድ ርክክብ መፈጸማቸውን አመልክቷል።
በክልሉ ለበርካታ ባለሃብቶች ተሰጥቷል በተባለ ተደራራቢ የመሬት ርክክብ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢያበድርም ገንዘቡ የገባበት አለመታወቁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በመንግስታዊ ባንኩ ላይ ደርሷል የተባለን ኪሳራ ተከትሎም ባንኩ ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች የሚሰጠውን ብድር ያቋረጠ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግስትም የመሬት ቅርምት ነው የተባለውን መሬት ለባለሃብቶች የመስጠት ስራ እንዲቀር ወስኗል።
ከመንግስት ብድርን የተረከቡ በርካታ ባለሃብቶችም ከወሰዱት ብድር ጋር ከሃገር መኮብለላቸውን የልማት ባንኩ ሃላፊዎች በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment