Monday, April 4, 2016

ህወሃቶች ስልጣኑን እሰከ ያዙት ድረስ አማራ ክልል ሊለማ አይችልም ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

መጋቢት ፳፮( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በደባርቅ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ከደባርቅ በየዳ ላይ የሚሰራው መንገድ መዘግየቱ በርካታ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸው፣ በክልሉ ለሚታየው የስራ መጓተትና ሁዋላ ቀርነት ህወሃትን ተጠያቂ አድርገዋል።

“የመንገዱ ስራ የሚከናወነው አኪር ኮንስትራክሽን በተባለ ተቋራጭ ሲሆን ድርጅቱ ለረዢም ጊዜ ስራውን ቢያዘገይም ማንም እንዲጨርስ ያስገደደው የለም፡፡” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች የከተማዋና የወረዳው አመራሮች በተቋራጭ ድርጅቱ ላይ በተደጋጋሚ ግፊት እንዲደረግበት የክልሉን መንግስት ቢጠይቁም፤የክልሉ መንግስት ግን ጉዳዩን ተከታትሎ ለመፈጸም የሚያሳየው ተነሳሽነት እንደሌለ በምሬት ተናግረዋል፡፡

“አኪር ኮንስትራክሽን ማለት የህውሃት የመንገድ ስራ ድርጅት በመሆኑ ጠያቂ የለውም፡፡” በማለት የሚከሱት ቅሬታ አቅራቢ አኪር የመንገድ ስራ ድርጅት አወጣኸኝ ኪሮስ በተባለ የህውሃት አባል የሚመራ በመሆኑና የህውሃት አመራር መንገዱ እንዲዘገይ የሚያደርጉትን የውስጥ ለውስጥ ሴራ ቢያውቁም የአማራ ክልል አመራሮች አስተያየት ከመስጠት በመቆጠብ በዝምታ ለማየት መገደዳቸውን በድፍረት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
“ይህን የመንገድ ስራ የሚሰራው ድርጅት የአማራ ተወላጆች ፕሮጀክት ቢሆን ኖሮ እስካሁን ይታስሩ ነበር፡፡” ያሉት ተናጋሪ የክልሉ መንግስት ፍርሃቱን አቁሞ መፍትሄ ያመጣ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡
“በክልሉ ያሉ አመራሮች ሆኑ በፌደራል ደረጃ አማራውን እንወክላለን የሚሉት አመራሮች ትክክለኛ የአማራ ተወላጆች ባለመሆናቸው የክልሉ እድገት እንዴት ይመጣል?” በማለት የጠየቁትና በመድረክ መሪዎች ንግግራቸው እንዲቋረጥ የተዋከቡት ተናጋሪ “የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራር ሊሆኑ የሚገባቸው የአማራ ተወላጆች መሆን ሲገባቸው፤እስከ አሁን ግን በተግባር የምናያቸው ከትናንሽ ከተሞች ጀምሮ እስከ ታላላቅ የሃገሪቱ ቦታዎች አማራውን ወክለው ቁልፍ ቦታዎችን የያዙት የክልሉ ተወላጆች አለመሆናቸው ልማቱ እንዳይፋጠን አድርጓል፡፡” በማለት መነጋገሪያቸው በመድረክ መሪው እስኪነጠቅ ድረስ በኃይል ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
በየአካባቢው በሚሰሩ የመንገድ ስራዎች ዙሪያ ፖለቲካዊ ተንኮሎች እንዳሉበት አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላው ተሰብሳቢ የወልቃይትን አካባቢዎች ከአማራ ክልል ከተሞች ጋር የሚያገኙት መንገዶች ሆን ተብሎ እንዲጓተቱ የማድረጉ ሴራ መቀጠሉን አጋልጠዋል፡፡
“በወልቃይትና አካባቢው የሚመረተው ከፍተኛ የሠሊጥ ምርት በአማራ ክልል እንዳያልፍ፣ከጎንደር ጋር ከፍተኛ የንግድ ትስስር የነበረውን ህዝብ ለማለያየት በማሰብ ከአምስት አመት በፊት የተጠናው መንገድ አሁንም እንዳይሰራ ሲደረግ የአማራ ክልል መንግስት በዝምታ ማየቱ ለክልሉ የሚያስብሰው እንደሌለ ያሳያል፡፡” በማለት የክልሉ ባለስልጣናት የክልሉን ጠረፋማ ወረዳዎች ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ላይ መሆናቸውን ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
“ከፍተኛ ውጣ ውረድ ያለባቸው የትግራይ ጠረፋማ የወረዳ ቀበሌዎች ግን ምርቱን ማስተላለፍ እንዲችሉ የመንገድ አውታሩ በፍጥነት እየተዘረጋላቸው ነው፡፡” በማለት የሚሰራው አድሎአዊ አካሄድ አይን ያወጣ ያንድ አካባቢና የተወሰኑ ቡድኖች ተጠቃሚነት እየጎላ መሄዱን ሲቃወሙ ተሰምተዋል፡፡
በአማራ ክልል የመንገድ እና የህንጻ ግንባታ ስራዎች አብዛኛውን ሰራ በመስራት ላይ ያሉት የህውሃት ድርጅቶች በርካታ ስራዎችን ሲያጓትቱ በተዋዋሉት መሰረት ባለመፈጸም ስራውን ሲያቋርጡ እና በተፈጸሙ ስራዎች የሚታዩ የግንባታ ስህተቶችን ሲፈጽሙ በዝምታ መታየታቸው አግባብ አለመሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው “ከብቸና ደጀን በመሰራት ላይ ያለውን የአስፋልት መንገድ ውል የወሰደው ሳት ኮንኮንስትራችሽን መንገዱን ከአምስት አመት በላይ በማጓተት ከፍተኛ ችግር ሲፈጥር ማንም ተው! ያለው የለም ፡፡ በማገልገል ላይ የነበረውን ድልድይ በአዲስ እሰራለሁ በማለት በማፍረስ ነዋሪውን ለችግር ቢዳርጉም ሁሉንም በዝምታ ታልፈዋል” በማለት በህውሃት ድርጅቶች በሚሰሩ ስራዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ማንም ደፍሮ አለመናገሩ የክልሉ አመራሮች ያላቸውን አቅም ውስንነት እንደሚያሳይ ይናገራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment