Monday, July 13, 2015

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አፍራሽ ግብረ ኃይል በከተማዋ ዳርቻ የሚገኙ የይዞታ ቦታዎች አፈረሰ

ሐምሌ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በርካታ ፖሊሶችና የታጠቁ ኃይሎች በመኪና በመሆን ከተማዋን ሲዞሩ መዋላቸውን ዘጋቢያችን ገልጻለች። የፖሊስ አባላት በተጠንቀቅ (stand by) ሆነው እዲጠብቱ የታዘዙ ሲሆን፣ ከአሁን በፊት ለምርጫ ቅስቀሳ በሚል ለባለ ይዞታ ቦታ ባለቤቶች የተሰጠው ጊዜያዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ከተቀማ በሁዋላ፣ ዛሬ ደግሞ ይባስ ብሎ አንዳንድ ቤቶችን በግዳጅ እያፈረሱ ነው። ህብረተሰቡ አመጽ ሊያስነሳ ይችላል በሚል የታጠቁ ሃይሎች ከተማውን እየዞሩና በሚፈርስበት አካባቢ እንዣበቡ እንደሚገኙም አክላ ገልጻለች።

በሌላ ዜና ደግሞ ከሁለት አመት በላይ ተደብቀው የተቀመጡት ከ2 ሺ በላይ ብስክሌቶች ለባሰ ብልሽት እየተዳረጉ መሆኑ ተገልጿል።
ከአሜሪካ እርዳታ ድርጅት (USAID) እና ከዓለም ባንክ (world bank) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በአማራ ክልል ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲውሉ የተላኩ ብስክሌቶች ሜዳ ላይ ተቀምጠው እየተበላሹ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ሰራኞች ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መንቀሳቀሻ እንዲውሉ ግብረ ሰናይ ሃገራትና ድርጅቶች የሰጡትን ድጋፍ፣ ቢሮው አገልግሎቱ በአግባቡ እንዲደርስ ባለመጣሩ ለክልሉ የቀረቡት ሁለት ሺህ ብስክሌቶች ርክክብ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ንብረቱ ለአንድ አመት በቢሮው ቅጥር ግቢ፤ ከዛም በኋላ ከህዝብ ዓይን በመሰወር በሽምብጥ ክፍለ ከተማ የግለሰብ ቤት ግቢ ውስጥ ለአንድ አመት ያክል እንዲቀመጥ ተደርጓል።
‹‹ ብስክሌቶችን ላለመረከብ የቀረቡት ምክንያቶች በቂና አሳማኝ ካለመሆናቸውም ሌላ ከፌደራል መንግስት ንብረቱን ለመመልከት የመጡት ባለሙያዎች በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ‘ንብረቱ ለብልሽት እንዳይዳረግ ለተጠቃሚዎች በአስቸኳይ ይተላለፉ!’ ቢሉም ፣ የጤና ጥበቃ ቢሮው አመራሮች ግን ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመግፋት ንብረቱ ለብልሽት ተዳርገዋል፡›› በማለት ቅሬታቸውን ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
ከሐያ ሽህ በላይ ብስክሌቶችን በመላ ሃገሪቱ ለማከፋፈል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ውል የወሰደው ‘ይርጋ ትሬዲንግ’ ሃላፊ አቶ ታደሰ ይርጋ ከአንድ ዓመት በፊት በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ‹‹ቀሩ የሚባሉት ዕቃዎች ብስክሌቶቹ አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያግዱ አይደሉም፡፡ቀሩ የሚባሉት ንብረቶች እስኪቀርቡ ገንዘብ በመያዣነት ሊያስቀሩ ይችላሉ፤ እንጅ በርካታ ሃብት የፈሰሰባቸውን የህዝብና የሃገር ሃብት ሜዳ ላይ በትነው ለብልሽት መዳረጉ በህግ ያስጠይቃቸዋል፡፡›› ብለዋል።

No comments:

Post a Comment