Thursday, July 2, 2015

የኢትዮጵያ ፓርላማ የምርጫ ቦርድ ቁልፍ ሰው የነበሩትን ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔርን የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮምሽን ኮምሽነር አድርጎ ሾመ፡፡

ሰኔ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዶ/ር አዲሱ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ቢሆኑም ከህወሃት/ኢህአዴግ ቀጥተኛ መመሪያ በመቀበልና በማስፈጸም ረገድ ቁልፍ ሰው መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተለይ ተቃዋሚዎች እንዲዳከሙና ትንንሽ ልዩነቶቻቸውን በማጦዝ ፓርቲዎች እንዲናጉና እንዲፈርሱ ከኢህአዴግ ጋር እየተናበቡ የሚሰሩ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትንም አቤቱታ በማድበስበስ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፤
ዶ/ር አዲሱ የሚሰጡዋቸውን መመሪያ ተከትለው ከማስፈጸምና ይህንንም የቦርዱ ውሳኔ በማስመሰል ለመገናኛ ብዙሃን ከመናገር በላይ አቅም እንደሌላቸው የጠቆሙት ምንጮቹ ብዙውን ጊዜ ዶክተሩ፣ ፕሮፌሰር መርጋን ከፊት ለፊት በማጋፈጥ ከጀርባ ሆኖ መስራትን የሚመርጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የምርጫ ቦርድ አባላት በጠ/ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማው የሚሾሙ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህ የቦርድ አባላት መካከል ግማሽ ያህሉ እንኩዋን ብቁ ተሳትፎ እንደሌላቸው ነገር ግን የሚሰጡ ውሳኔዎች እየተላከላቸው
እንደሚፈርሙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህ ክንውን ደግሞ በዶ/ር አዲሱ የሚፈጸም ነው ተብሎአል፡፡
ዶ/ሩ በቦርዱ ከተሾሙ በሃላ ሁለት ምርጫዎችን በማስፈጸም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ 99 ነጥብ 6 እና 100 በ 100 እንዲያሸንፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ፣ የዛሬው ሹመት ለዚህ ውለታ የተሰጠ ሳይሆን እንደማይቀር ዘጋቢያችን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን በኮምሽነርነት ሲመሩ የቆዩት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ፣ በተለይ ኢትዮጵያ የምትወቀስባቸውና የምትታወቅባቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደጋግመው በመካድ የሚታወቁ ሲሆን በተለይ የእስረኞች አያያዝና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት «ቦታው ድረስ ሄደን አረጋግጠን ችግር የለባቸውም» በማለት በተደጋጋሚ የመንግስትን ድክመት በመከላከል የሚታወቁና የኢህአዴግ ባለውለታ ናቸው።


No comments:

Post a Comment