Friday, July 10, 2015

ወያኔ አርበኞች ግንቦት 7 ጥቃት እንደሰነዘረበት አመነ

ሰሞኑን የአርበኞች ግንቦት 7 የነጻነት ታጋዮች በትግራይ እና በወልቃይት-ጠገዴ በተለያዩ ቦታዎች በወያኔ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ የሽምቅ ውጊያ ጥቃት መሰንዘራቸውን በቃል-አቀባያቸው አማካኝነት ለኢሳት ቴሌቪዥን እና ራድዮ ሲገልጹ ሰንብተዋል።

ዜናው በኢሳትና በተለያዩ የማህበራዊ ድረገጾች በስፋት ሲሰራጭ በነበረበት ወቅት ዝምታን መርጦ የነበረው ወያኔ ኋላ ላይ የተዛቡ መረጃዎችን ሲያሰራጭ ከርሞ ዛሬ በራድዮ ፋና አማካኝነት አርበኞች ግንቦት 7 ጥቃት እንደሰነዘረበት ለማመን ተገዷል።

ራድዮ ፋና ባሰራጨው ዜና “ከሰላሳ የማይበልጡ የሻብያ ተላላኪዎች ከኤርትራ በሚያዋስነን ድንበር አካባቢ ሰርገው ለመግባት ሲሞክሩ ተደምስሰዋል” ብሏል።

ይሁንና ራድዮ ፋና በዜና ዘገባው ግጭቱ የተፈጠረባቸውን ቦታዎች እና ጊዜ ሳይጠቅስ ማለፍን መርጧል።

አርበኞች ግንቦት 7 በበኩሉ በትግራይ በተለያዩ ቦታዎች እና በወልቃይት-ጠገዴ አካባቢ በሰነዘረው ድንገተኛ ጥቃት መኮንኖችን ጨምሮ በርካታ የወያኔ ሰራዊት አባላትን መግደሉን አስታውቋል።

አርበኞች ግንቦት 7 በሰነዘረው ድንገተኛ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የወያኔ ሰራዊት አባላት የጤና ጣብያዎችን አጨናንቀው እንደከረሙ የአካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን ወያኔ ጉዳት የደረሰባቸውን ክፍለ ጦሮቹን በሰው ሃይል ለማጠናከር በብዙ አውቶቢሶች የታጨቁ የሰራዊት አባላቱን ግጭቶቹ ወደተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ሲያጓጉዝ እንደሰነበተ የአይን እማኞች ተናግረዋል።


No comments:

Post a Comment