Friday, July 24, 2015

ፕ/ት ኦባማ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለኢትዮጵያ መሪዎች ያነሳሉ ብለው እንደሚጠብቁ የሂውማን ራይትስ ወች ባለስልጣን ገለጹ

ሐምሌ ፲፸ (አስራሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ሌስሊ ሌፍኮ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብአዊ መብት ጥሰት የፕሬዚዳንቱ አንድ አጀንዳ ይሆናል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ፕ/ት ኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኘት አልነበረባቸውም የሚለው አስተያየት ዋናው ጉዳይ አለመሆኑን የገለጹት ሌፍኮው፣ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ምን ምን ጉዳዮችን አነሱ የሚለው ጥያቄ ዋናው ጉዳይ መሆን እንደሚገባውና የጉብኝታቸው ውጤት ፣ በሁዋላ ላይ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚፈጽማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች የሚያስጠይቀው መሆኑን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ ፕሬዚዳንቱ ሰራዊቱ ተጠያቂነት እንዲኖረው ጫና እንዲያደርጉ ድርጅታቸው ከሌሎች የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጋር በመሆኑን መጠየቁንም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያና በኬንያ በሚያደርጉት ጉብኝት ስለተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ መብት መልዕክት እንደሚያስተላልፉ አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሳወቁት ፤ በአፍሪካ ጉብኝታቸውና በሌሎች ጉዳይች ዙሪያ ከቢቢሲው ጆን ሶፔል ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው። ኦባማ በተመሳሳይ ጾታ ተጓዳኞች ዙሪያ እየተፈጸመው ያለው መገለል በሚቀርበትና መብታቸው በሚከበርበት ዙሪያ ለአፍሪካ መሪዎች መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል። “እየሄዱ ያሉት በፓርላማዋ አንድም የተቃዋሚ ተወካይ ወደሌለባት ኢትዮጵያ እኮ ነው” በማለት ጆን ሶፔል ሲያነሳባቸው፤ “አዎ፤እሱን አውቃለሁ” በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በጉዟቸው የሰብዓዊ መብቶች በሚጠበቁበትና ለሲቪል ማህበረሰቡ እንቅስቃሴ በሮች በሚከፈቱበት ዙሪያ እንደሚነጋገሩና ይህም የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በበርማ ያደረጉትን ጉብኝት ምሳሌ በመጥቀስ አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው በ አካባቢው ደህንነትና በአፍሪካ እያደገ በመጣው የቻይና ኢንቨስትመንት ዙሪያም ከህብረቱ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ጠቁመዋል።

No comments:

Post a Comment