Monday, July 13, 2015

በዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ የሚመራው የምርት ገበያ ድርጅቱ በመተማና አብርሃ ጅራ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን በመዝጋት ወደ ጎንደር ከተማ ለማዛወር እቅድ እንዳለው ምንጮች ገልጸዋል።

ሐምሌ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ሰሞኑን በአርበኞች ግንቦት7 እና በገዢው ፓርቲ ወታደሮች መካከል የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ በዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ የሚመራው የምርት ገበያ ድርጅቱ በመተማና አብርሃ ጅራ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን በመዝጋት ወደ ጎንደር ከተማ ለማዛወር እቅድ እንዳለው ምንጮች ገልጸዋል። ድርጅቱ በሰሜን አካባቢ በሁመራ፣ ጎንደርና መተማ ለሰሊጥ ጥራት ምደባና ማከማቻ ቅርንጮፎችን የከፈተ ሲሆን፣ የአብርሃ ጅራ ቅርንጫፍ በዚህ ዓመት የተከፈተ ነበር። ድርጅቱ በእነዚህ ከተሞች ያለውን ቅርንጫፍ ለመዝጋቱ እስካሁን የሰጠው ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም፣ ምንጮች እንደሚሉት ግን በአካባቢው እየታየ የመታው አለመረጋጋት እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ሳያደርገው አልቀረም። የፌደራል ፖሊስ በወልቃይት "ሰርጎ-ገቦች" ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር። አርበኞች ግንቦት7 በወሰደው ድንገተኛ ጥቃት በርካታ የስርዓቱን ወታደሮች መግደሉን አስታውቋል። ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ጥቃቱን አክሽፌዋለሁ ሲል መግለጫ ሰጥቷል። የአርበኞች ግንቦት7 ሃይል ጥቃቱ እንደማይቆምና አድማሱን እያሰፋ እንደሚሄድ አስጠንቅቋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ በኩል የሚሰነዘረው ትንኮሳ ካልቆመ፣ መንግስታችን ለህዝብ ነግሮ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል። በኢትዮጵያ በኩል አየር ሃይሉ በተጠንቀቅ እንዲቆም ከመታዘዙ በተጨማሪ፣ የአዳዲስ ወታደሮች ምልመላና ከፍተኛ ወታደራዊ ልምምድም እየተካሄደ ነው። በኤርትራ በኩል እስካሁን በጉልህ የሚታይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment