Wednesday, July 22, 2015

አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔውን የሱር ኮንስትራክሽንን ንብረት ማውደሙን ገለጸ ፣ጦርነቱ በጎንደር አካባቢ ልዩ ወረዳዎች ቀጥሏል

Ginbot7_arebegnochi1

የአርበኞች ግንቦት 7 ህዝብ ግንኙነት ጋዜጣዊ መግለጫ:- የአርበኞች ግንቦት 7 ጀግና የነፃነት ፋኖዎች በኢትዮጵያ መሬት ላይ በህዝቡ ጉያ ውስጥ ሆነው በወልቃይት የጀመሩትን ወታደራዊ ጥቃት አሁንም አጠናክረው በመቀጠል የህወሓትን አገዛዝ እያሽመደመዱት ነው፡፡ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የተባለውን በቁሙ ደርቆ የበሰበሰ ዛፍ ከስሩ ገዝግዞ ለመቁረጥ የተጀመረው ትግል ሰሞኑን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ከወታደራዊ ጥቅምና ደህንነት አንፃር ስማቸውን ለመግለፅ በማይቻልባቸው የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ላይ በሚንቀሳቀሰው የህወሓት ፀረ-ሽምቅና ሚሊሻ ኃይል ላይ ደፈጣ በመጣል ደምስሰውታል፡፡ በአዘዞ እና ጠዳ ከተሞች መካከል ከሚገኘው መገጭ ወንዝ አጠገብ በግንባታ ስራ ላይ የነበረው የሱር ኮንስትራክሽን የድንጋይ መፍጫ ማሽነሪዎች እና ሌሎችን የግንባታ ቁሳቁሶች በአርበኞች ግንቦት 7 አርበኛ ታጋዮች ሙሉ በሙሉ በመውደሙ ስራውን አቁሞ እንዲሸሽ ተገዷል፡፡ ሱር ኮንስትራክሽን የህወሓቶች የግል ንብረት የሆነው ኤፈርት በስሩ ካሉት ከ60 በላይ የንግድ ኩባንያዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሱር ኮንስትራክሽን ውድመት በደረሰበት አካባቢ የግንባታ ስራውን በብቸኝነት የያዘው እንደተለመደው ያልምንም ጨረታ ነው፡፡ በተያያዘ ዜና ከዚያው ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ውስጥ የሚኖር አቶ ጎሸ ሽባባው የተባለ ገበሬ ለአርበኞች ግንቦት 7 አርበኛ ታጋዮች ስንቅ አቀብለሃል በሚል በህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውሎ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበታል፡፡ አቶ ጎሸ ሽባባው አሁን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት እስር ቤት ውስጥ ይገኛል፡፡ በላይ አርማጭሆ አንገረባ ቀበሌ የአርበኞች ግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች እና የህወሓት ጸረ-ሽምቅ ኃይል ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ጦርነት አድርገዋል፡፡ ጦርነቱም የተካሄደው ሀምሌ 11 2007 ዓ.ም ሲሆን በአካባቢው ለአሰሳ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የህወሓት ፀረ-ሽምቅ ኃይል በውስጥ አርበኞች የተከፈተበትን ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃት መቋቋም ስላልቻለ አንድ ሰዓት ከፈጀ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ለጊዜው ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ በርካታ አባላቱ ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ የሱዳን መከላከያ ኃይል የኢትዮጵያን ወሰን ጥሶ ገብቶ ከሆር ሁመር ገበሬዎች ጋር መታኮሱ ታውቋል፡፡ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ 2 ገበሬዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በአካባቢው ሰፍሮ የሚገኘው ህወሓት መራሹ መከላከያ ሰራዊት የሱዳን መከላከያ ኃይል ድንበር ሰብሮ ገብቶ በገበሬው ህዝብ ላይ የጦር ጥቃት ሲያደርስ እየተመለከተ እንዳላየ በዝምታ አልፎታል፡፡

No comments:

Post a Comment