Friday, July 17, 2015

በጋሞ ጎፋ ዞና ኢህአዴግ ባለስልጣናት በእርስ በርስ ሽኩቻ እየታመሱ ነው

ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት ችግሩ የተፈጠረው በጋሞና በጎፋ ተወላጅ ባለስልጣኖች መካካል ነው። የዞኑን፣ የክልሉንና የፌደራል ስልጣኑን የተቆጣጠሩት የጎፋ ተወላጅ ባለስልጣኖች፣ ጋሞዎችን ሰድበዋል ፣ የጋሞ ተወላጅ ባለስልጣናትን በንቀት ያያሉ በሚል እርስ በርስ በጀመሩት ቁርሾ፣ የመንግስት ስራ የተስተጓጎለ ሲሆን፣ የእርስ በርስ ሽኩቻውን ወደ ህዝብ በመውሰድ የጋሞ ባለስልጣናት የጋሞ ተወላጆችን አሰባስበው ለነገ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ እቅድ ይዘዋል። የጋሞ ባለስልጣናት ደጋፊዎቻቸውን ከገጠር ማስመጣታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ ተስፋየ ቤልጂጌ፣ ጥላሁን ከበደና ሌሎች የክልልና ዞን ባለስልጣናት እንዲወርዱላቸው ይጠይቃሉ። ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለዘመናት ተቻችለው የኖሩትን ሁለቱን ህዝቦች በሚከፋፍለው ሴራ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል፣ ተቃውሞው በእርሳቸውም ላይ እንደሚካሄድ ምንጮች ገልጸዋል። የአካባቢው የኢህአዴግ ሹሞች እርስ በርስ የሚካሂዱት ሽኩቻ መጠኑን አስፍቶ ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳያመራ ስጋት መፈጠሩን ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ቅዳሜ የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ እውቅና ያግኝ አያግኝ የታወቀ ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment