Monday, July 6, 2015

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት 

«ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት እንደተዘዋወርኩ ከጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና አበበ ቀስቶ ጋር ነበርን፡፡ ከጥቂት ጊዜያቶች በኋላ አበበ ቀስቶ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወር ውብሸት ታዬ ወደ ሌላ ዞን ተቀየሯል፡፡ ዛሬ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በማንም እንዳይጎበኝ ተከልክሏል፡፡ እኔም ለተወሰኑ ወራት በማንም እንዳልጎበኝ እግድ ተጥሎብኝ እንደነበር ታውቃላችሁ፡፡ በኋላ ላይ ቤተሰቦቼ እና ወዳጆቼ እንዲጠይቁኝ ተፈቅዶ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን ከአዲስ አበባ የመጡ ጠያቂዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ዛሬም እናንተን እንዴት እንዳስገቧችሁ እንጃ፡፡»

«ምንም እንኳ የእስር ቤት መልካም ባይኖረውም ይህ ግቢ ፋሺዝም የነገሰበት ማረሚያ ቤት ነው፡፡ ማረሚያ ቤት የሰዎችን እኩይ ባህሪ ለማረምና ለማስተካከል የታነፀ ቢሆንም ይህ ማረሚያ ቤት የትኛውንም ታራሚ ለማረም ብቁ አይደለም፡፡ መሰረታዊ ነገሮች አልተሟሉበትም፡፡ ውሃ ከ3 ተከታታይ ቀናት በላይ ይጠፋል፡፡ ታራሚዎች እነዚህን ጉድለቶች በራሳቸው ገንዘብ ገዝተው እንዳይጠቀሙ እንኳ በወር ከ200 ብር የበለጠ ከቤተሰብ እንድንቀበል አይፈቀድልንም፡፡ ከተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የሚመጡ ታራሚዎች እዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ምግብ የሚያስገባላቸው ቤተሰብ በአቅራቢያቸው የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች በገንዘባቸው ገዝተው እንዳይጠቀሙ እንኳ በወር ከ200 ብር በላይ እንዳይቀበሉ ስለተከለከሉ ከፍተኛ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡»

«እኔ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወርኩ አንስቶ በግቢው ውስጥ የሚገኘው ቤተመጻሕፍት አገልግሎት እንዳይሰጥ ሆኗል፡፡ የእስር ጊዜን በንባብ ማሳለፍ አለመቻል በጣም ከባድ ነው፡፡ ቤተሰቦቼና ወዳጆቼ የሚያመጡልኝ ማንኛውንም አይነት መጻሕፍቶች ሊገባልኝ አልተፈቀደም፡፡ ፖለቲካ ነክ ከሆኑ መጽሓፍት ውጪ ያሉትን የልብወለድ መጽሓፍቶች እንኳ እንዳይገባ ተከልክሏል፡፡ እዚህ ያለው አብዛኛው ታራሚ ማንበብ ይፈልጋል፡፡ ከመከልከሉ በፊት ታራሚዎች እጅ ላይ ያሉት ጥቂት መጻሕፍቶችን ሁሉም ተቀባብሎ አንብቦ ጨርሷቸዋል፡፡ ንባብ የማረምና የመለወጥ አቅም አለው፤ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎች በንባብ ጊዜያቸውን እንዳያሳልፉና እንዳይለወጡ አድርጓል፡፡»

«በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ታራሚዎች ከእኔ ጋር እንዳይሆኑ ተከልክለዋል፡፡ ብዙዎች ሊያወሩኝና አብረውኝ ሊሆኑ እንኳ ቢፈልጉ የሚደርስባቸውን ቅጣት በማሰብ ሊቀርቡኝ አይደፍሩም፡፡ ከእኔ ጋር ሆነው የታዩ ሁሉ በጨለማ ቤት ውስጥ እንዲታሰሩ ይደረጋሉ፡፡ ያለብኝን የጀርባ እና የጆሮ ህመም መታከም አልቻልኩም፡፡ እነዚህና ተመሳሳይ ጭቆናዎች እኔ ከማምንበትና እከተለው ከነበረው አካሄድ መደ ኋላ አይመልሱኝም፡፡ በፊት የተናገርኩትን ዛሬም እደግመዋለሁ፤ ጉዟችን እስከ ቀራንዮ ድረስ ነው፡፡»
(ከተመስገን ደሳለኝ ጋር ከነበረን አጭር ቆይታ መካከል ቃል በቃል ያልተወሰደ)


No comments:

Post a Comment