Tuesday, July 12, 2016

የወልቃይት ጥያቄ የሚመሩ የኮሚቴ አባላትን ለመያዝ በተወሰደው ዕርምጃ የሰላማዊ ሰው ህይወት ጠፋ

ኢሳት (ሃምሌ 5 ፥ 2008)
የወልቃይት የማንነት ጥያቄን የሚመሩ የኮሜቴ አባላትን ለማሰር በተወስደ እርምጃ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከፍተኛ ግጭት አስከተለ። ሰላማዊ ሰዎችም የተገደሉ ሲሆን፣ ከህዝብ ወገን በተወሰደ አጸፋ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውም ታውቋል። የኮሚቴ አባል የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ
ዘውዴ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተከበዋል።




መንግስት በዕለቱ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ሶስት የልዩ ሃይል ፖሊሶች ሲገደሉ፣ 5 መቁሰላቸው አስታውቋል።
አንድ ሰላማዊ ሰው መገደሉንም አስታውቋል። ሆኖም መንግስት ዕርምጃውን ለመውሰድ የተንቀሳቀሰም በወልቃይት ማንነት ጥያቄ ባነሱ ኮሜቴ አባላት ላይ መሆኑን አላመነም።
ከተፈላጊዎቹ ውስጥ አንደኛው ሲያመልጡ አንደኛው መታኮሳቸውን የገለጸው የብሄራዊ መረጃና የጸረሽብር ግብረ ሃይል፣ ሲታኮሱ የነበሩት በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው የሰጠው መግለጫ የለም።
የብሄራዊ መረጃና የፌዴራል ፖሊስ በስም ያልጠቀሳቸው ሆነም፣ በይፋ እጅ አልሰጥም ብለው በመታኮስ ላይ የሚገኙት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ መሆናቸው ታውቋል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄን አንግበው ከሚንቀሳቀሱ የኮሚቴ አባላት አንዱ ናቸው። ማክሰኞ ሌሊት ከ11 ሰዓት ጀምሮ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ያነሱ የኮሚቴ አባላትን ለመያዝ የተንቀሳቀሰውና ከትግራይ ተነሳ የተባለው ቡድን ከአማራ ክልላዊ መንግስት እውቅና ውጭ መንቀሳቀሱም ተሰምቷል።
ከኮሚቴ ኣባላት አቶ አታላይ ዘርፌ አቶ ጌታቸው አደመ አቶ መብራቱ ጌታሁንና አቶ አለነ ሻማ የተያዙ ሲሆን፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ በህግ የምትፈልጉኝ ከሆነ ሲነጋ መምጣት ትችላላችሁ በማለታቸው በተፈጠረው ግጭት አለመግባባትና በግድ እጅ እንዲሰጡ በመንቀሳቀሳቸው ኮሎኔሉ ዕርምጃ መውሰዳቸው ተመልክቷል።
እርሳቸውን ለመያዝ ተጨማሪ ሃይል ወደ አካባቢው መንቀሳቀሱን ተከትሎ የጎንደር ከተማ ህዝብ ዕርሳቸው ለመታደግ መንገድ ዘግቶ በመኖሪያቸው አካባቢ እየጠበቃቸው ይገኛል።
በቁጣ የተነሱ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ጎንደር የሚመላለሰውን የህወሃት ንብረት የሆነውን ሰላም አውቶቡስን ያቃጠሉ ሲሆን፣ በርካታ ንግድ ቤቶችም መውደማቸው ታውቋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን ለመታደግ የወልቃይት ተወላጆች ከጎንደር ከተማ በዕለቱ ማምሻውን ገብተዋል። ዘመዶቻቸው አግባብተን እጅ እንዲሰጥ እናደርጋለን በማለት ከተቀላቀሏቸው በኋላ በጋራ አፈሙዛቸውን በመንግስት ሃይሎች ላይ ማዞራቸውም ተሰምቷል።
እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት የተኩስ ድምፅ እየተሰማ ሲሆን የከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች በድንጋይና ምሰሶ እንጨት ተዘግቷል።
በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተከትሎ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ባለስልጣናት በአማራ ክልል አንዳንድ ባለስልጣኖች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን የደህንነት ምንጮች እየገለጹ ሲሆን፣ በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎችም እንቅስቃሴዎች በመታየት ላይ ይገኛሉ።
የአማራ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ አንዳንድ የክልል ባለስልጣናት ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ማድረግ አልቻሉም በሚል ከህወሃት ወገን ወቀሳ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።

No comments:

Post a Comment