Friday, July 22, 2016

በኢትዮጵያ የሚደረጉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተባለ

ኢሳት (ሃምሌ 15 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ እና በተለያዩ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በሂደት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አርብ አሳሰበ።
መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገውና በሃገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎችን ዙሪያ ሪፖርቱን ያወጣው ፍሪደም ሃውስ፣ መንግስት በብቸኝነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁጥጥርን ተግባራዊ ማድረጉ ተቃውሞዎች እንዲቀሰቀሱና እየተባባሱ እንዲሄድ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ አማራና የደቡብ ክልል መዛመቱን ያወሳው ድርጅቱ፣ መንግስት ድርጊቱን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው እርምጃ በሃገሪቱ ያለውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አደጋ ውስጥ እንደከተተው ገልጿል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት አማራጭ የሆኑ የፖለቲካ አመለካከቶች እንዳይበራከቱ ለማድረግ እየወሰደ ያለው አፈናና ቁጥጥር በርካታ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ ምክንያት ሆኖ መገኘቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።
በሃገሪቱ በተደጋጋሚ በመካሄድ ላይ ያሉት እነዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በሂደት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ እንደሚችል በፍሪደም ሃውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ሃላፊ የሆኑት ጄኒፈር ቻሬቲ በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ ባሰፈሩት ጽሁፍ አሳስበዋል።
ገዢው የኢህአዴግ መንግስት የፓርላማ መቀመጫን በብቸኝነት እንዳሸነፈ ካሳወቀ ከስድስት ወር በኋላ ሃገሪቱ በመካሄድ ላይ ያሉት እንደዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በአጠቃላይ ለሃገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ሃላፊዋ ገልጸዋል።
ከህዝብ ለሚነሱ የተለያዩ ፖለቲካዊና የብሄር ጥያቄዎች ምላሽን የማይሰጥ መንግስት ዘላቂ ልማትን ሊያካሄድ አይችልም ሲሉ ያስታወቁት ጀኒፈር ቻሪቴ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን አመልክቷል። በቅርቡ ተመሳሳይ ሪፖርትን አውጥቶ የነበረው ሂውማን ራይትስ ዎች በክልሉ ለወራት ከዘለቀው ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ወደ 400 ሰዎች አካባቢ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
መንግስት በሃገሪቱ ባሉ የሲቪል ማንገረሰብ ተቋማት ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢገኝም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተቋማቱ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ እድገት ላይ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ማንነታቸው ሊያረጋግጥ መቻሉን ፍሪደም ሃውስ ያካሄደውን ጥናት ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አስፍሯል።

No comments:

Post a Comment