Friday, July 22, 2016

የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ስርጭት ተቋረጠ

ኢሳት (ሃምሌ 15 ፥ 2008)

የአማራ ክልል ቴለቪዥን የሳተላይት ስርጭት መቋረጡን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ጉዳዩ ከክፍያ ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክቷል። ሆኖም አንዳንድ ምንጮች የስርጭቱን መቋረጥ ከጎንደር ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጋር አያይዘውታል።

የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ከጎንደር ህዝባዊ እንቅስቃሴና ከወልቃይት የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የመንግስት ባለስልጣናት የመብት ጠያቂዎቹን በሚወነጅሉበት መጠን አለመስራቱንና ህዝብን ከሚያስቆጡ ድርጊቶች መቆጠቡ ለስርጭቱ መቋረጥ እንደምክንያት እየተጠቀሰ ይገኛል።
የክልሉ መንግስት የሳተላይት ክፍያውን ለኢትዮ-ቴሌኮም መከፈሉን ሆኖም፣ ኢትዮ-ቴሌኮም ክፍያውን ለሳተላይት ኩባንያው ባለመከፈሉ ስርጭቱ መቋረጡን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ አስታውቋል። በህወሃት ም/ሊቀመንበርና በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በሆኑት በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካዔል ስር የሚገኘው የኢትዮ-ቴሌኮም ክፍያውን ያልፈጸመበት ምክንያት አልታወቀም። ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም ኢትዮ-ቴሌኮም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ አልሰጠም።
የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ባለፉት 2 አመታት ለኢትዮ-ቴለኮም የከፈልነው ክፍያም ከሳተላይት አቅራቢ ኩባንያ አልተዳደርም በማለት መግለጫ መስጠቱ አነጋጋሪ ሆኖ ተገኝቷል።

No comments:

Post a Comment