Friday, July 8, 2016

የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም በሶማሊያ ቆይታውን አራዘመ ውሳኔውን ሂውማን ራይትስ ወች አወገዘ

ሐም ( አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ያመጣል ተብሎ ወደ ሶማሊያ ያመራው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም  በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንዳልቻለ ተገልጿል። የኅብረቱ ጦር ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ 22 ሽህ ሰራዊቶች ቢኖሩትም እስከ 2018 እ.ኤ.አ. በአገሪቱ ተልእኮውን አጠናቆ ለሶማሊያ ጦር አስረክቦ ይወጣል ሲባል የቆየ ቢሆንም ከአልሸባብ ተዋጊዎች በገጠሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች የመቆያ ጊዜውን እስከ 2020 እ.ኤ.አ.  ድረስ ለማራዘም ተገዷል።

በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ፍቃድ 2007 እ.ኤ.አ. የተቋቋመውን አሚሶንን በዋናነት ሲረዳ የነበረው የአውሮፓ ኅብረት እገዛውን 20 % ለመቀነስ ውሳኔውን አሳልፏል። አልሸባብ ተገፍቶ የወጣባቸውን የገጠር አካባቢዎች ድጋሜ በእጁ በማስገባት ላይ ሲሆን ኡጋንዳና ኬኒያ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ተከትሎ በቀጣይ ዓመታት ሶማሊያን ለቀው እንደሚወጡ አስቀድመው አሳውቀዋል። በሶማሊያ ከተሰማሩት የሰላም አስከባሪ ጦር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ያላትና ስድስት ሽህ ሰራዊት ያሰማራችው ኡጋንዳ በ2017 እ.ኤ.አ. ሙሉ ለሙሉ ሶማሊያን ለቀው እንደሚወጡ የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይም ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ስለ ሞቱትና ቁስለኛ የሰራዊቱ አባላት እስካሁን የተገለጸ ይፋዊ አሃዝ ካለመኖሩ በተጨማሪ እንደ ሌሎች አገራት የክብር ብሄራዊ የቀብር ስነስርዓት አልተደረገላቸውም። የአሚሶም ወታደሮች በሶማሊያ በእየገጠማቸው ባለው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተስፋ እየቆረጡ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ሲሆን ላለፉት ስድስት ወራት በአውሮፓ ኅብረት ሲቆረጥላቸው የነበረው የውሎ አበል ደመወዛቸው እንዳልተከፈላቸውም  ኒውስ ዊክ አክሎ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በትናትናው እለት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶምን በሶማሊያ የመቆያ ጊዜ ማራዘሙን ተከትሎ ሂውማን ራይትስ ወች ወቀሳ አቀረበ። የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጦር በቆይታው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በመፈጸም በሶማሊያን ዜጎች ላይ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሶቶችን ፈጽሟል ሲል ሂውማን ራይትስ ወች ሪፖርት አቅርቧል።
የሕብረቱ ጦር አባላት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ግድያ፣ የወሲብ ጥቃቶችንና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያደርሱ ስለሆነ በገለልተኛ አጣሪ አካል ጉዳዩ ታይቶ አጥፊዎቹ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ብሏል። ወደ ሶማሊያ ጦራቸውን የላኩት የቀጠናው አገራት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በአገራቸው ውስጥም የሚፈጽሙ ስለሆኑ ከፖለቲካዊ ፍላጎት ይልቅ ለፍትሕ ቅድሚያ በመስጠት ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ሲል ጥሪውን አሰምቷል።

No comments:

Post a Comment