Tuesday, July 5, 2016

የኢትዮጵያ ጦር የጋላድ ከተማን ለቆ ወጣ

ሰኔ ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ የጦር መሳሪያ የታጠቁ የአልሸባብ ወታደሮች በማእከላዊ ሶማሊያ በጋለድቡ ክልል ውስጥ የምትገኘውን የጋላድ ከተማን ድጋሜ በቁጥጥር ስር አድርገዋል።

በስፍራው በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ስም የነበሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮችና የሶማሊያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸው ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች መሸሻቸውን ተከትሎ እኩለ ቀን ላይ የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎችና የከተማዋ አስተዳደሮች ሙሉ ለሙሉ እነሱን ተከትለው ከከተማዋ መውጣታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

የጋላድ ከተማን ፖሊስ ጣቢያና የከተማዋ አስተዳደር ጽሕፈትቤት በር ላይ ጥቁሩ የአልሸባብ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ እንደነበርም አክለው ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ካለምንም የመከላከል ውጊያ መሸሻቸውን ተከትሎ የአልሸባብ ወታደሮች ከተማዋን በእጃቸው አስገብተው የእሩምታ ተኩስ ከፍተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው በሚሸሹት በኢትዮጵያ ወታደሮችና አልሸባብ ታጣቂዎች መሃከል ጦርነት ይደረጋል ብለው በመስጋት ፍርሃት ላይ መውደቃቸውንም ገልጸዋል።
የጋላድ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በአልሸባብ እጅ መውደቅ የሕብረቱ የሰላም አስከባሪ ጦርና ለሶማሊያ ጦር ከፍተኛ አደጋ የሆነ እንቅፋት ከፊታቸው መደቁኑን ያመላክታል ሲል ኦል አፍሪካ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment