Thursday, July 14, 2016

አሜሪካና እንግሊዝ ዜጎቻቸው ወደ ጎንደር እንዳይሄዱ አሳሰቡ

ሐም ፯ ( ሰባት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ተቀማጨነቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሆነው የአሜሪካን ኤንባሲ አሜሪካዊያን ዜጎች ወደ ጎንደር ከተማና አካባቢው እንዳይጓዙ ጊዜያዊ የጉዞ እገዳ ጣለ። በተጨማሪም ኤንባሲው በጎንደር አካባቢ ያለው ሕዝባዊ አመጽ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ ወደ ቀጠናዎቹ እንዳይዘዋወርና በአሁኑ ወቅትም በስፍራው ያሉ ዜጎች እራሳቸውን እንዲጠብቁም ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

የእንግሊዝ ኤንባሲም በበኩሉ በጎንደር ያለው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን አመልክቶ እንግሊዛዊያን ወደ ከተማዋ እንዳይጓዙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶችም በአማራ ክልል ያለው የደህንነት ሁኔታዎች ሕዝባዊ ዓመጹን ተከትሎ እየከፋ መምጣቱን በመግለጽ ሰራተኞቻቸው ወደ አካባቢው እንዳይሰማሩ የጉዞ ማእቀብ ጥለዋል።

No comments:

Post a Comment