Wednesday, December 24, 2014

አቶ መላኩ ፈንታ ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ውሳኔ በማረሚያ ቤት እንዲነገራቸው ጠየቁ

-ሁለት ጠበቆች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ ተላለፈባቸው

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ጥብቅና የቆሙላቸውን ጠበቆች እንዲሰናበቱና የሚያርፍባቸውን ውሳኔ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲሰሙ፣ ክሱን እየመረመረው የሚገኘውን ፍርድ ቤት ትናንትና ጠየቁ፡፡

አቶ መላኩ ፈንታ ጥያቄውን ያቀረቡት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ልደታ ምድብ ችሎት ነው፡፡ አቶ መላኩ ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ውሳኔ ለመስማት ጥያቄ ለማቅረብ ያስገደዳቸው፣ አቶ ተሻገር ደሳለኝ የተባሉት ጠበቃቸው የምስክርንና የችሎቱን ክብር የሚነካ ንግግር እንዳደረጉ ፍርድ ቤቱ ገልጾ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠቱ ነው፡፡


ፍርድ ቤቱ በዕለቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ለአቶ መላኩ ጠበቃ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ ጠበቃ ለአቶ ሲሳይ ለምለም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የከሳሽ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ምስክር፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቢያነ ሕግ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እሸቱ ወልደ ሰማያት (በወቅቱ ተጠርጣሪ ሆነው በእስር መቆየታቸው ይታወሳል) በተለይ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል፣ ከቀረጥ ነፃ ስላስገባቸው ዕቃዎች ዳግም ቆጠራ ጋር በተያያዘ ከሰጡት የምስክርነት ቃል ነው፡፡

ጠበቆቹ ለምስክሩ፣ ኢንተርኮንቲኔንታል ልማታዊ ስለመሆኑ በመስቀለኛ ጥያቄ ሲያነሱላቸው ‹‹አልምቷልም አጥፍቷልም›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ምስክሩ ስለጥፋቱ ሊያብራሩ ሲጀምሩ፣ ጠበቆች ‹‹እኛ ስለጥፋቱ ያነሳነው ነገር የለም፤ እየጠየቅን ያለነው መስቀለኛ ጥያቄ በመሆኑ፣ ስላልጠየቅነው ነገር ምላሽ ሊሰጡ አይገባም፤›› የሚል መቃወሚያ ለችሎቱ አቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክሩ እንዲናገሩ በመፍቀዱ ጠበቆቹ ደግመው ሲቃወሙ፣ የፍርድ ቤቱንና የምስክሩን ክብር እንደነኩ በመግለጽ፣ ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲካሄድ የነበረው ምስክር የመስማት ሒደት ተቋርጦ፣ ክብር ነክተዋል በተባሉት ሁለት ጠበቆች ላይ ትናንትና ሁለት ጥብቅ ትዕዛዝ ፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በአዳር ትናንትና በሰጠው ትዕዛዝ እንዳብራራው፣ ምስክሩ ኢንተርኮንቲኔንታል አጥፍቷልም አልምቷልም ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለተሻለ ፍትሕ ይረዳል የሚል እምነት በመያዙ ምስክሩ ‹‹አጥፍቷልም›› በሚለው ላይ እንዲያብራሩ አዟል፡፡ ምስክሩ ማብራራት ሲጀምሩ፣ ጠበቆቹ ተቃውሞ እንዳላቸው ሲያመለክቱ እንደተፈቀደላቸው በትዕዛዙ አስፍሯል፡፡

ጠበቆቹ በተቃውሞአቸው ለችሎቱ የተናገሩት፣ ምስክሩ ምስክር እንጂ ዓቃቤ ሕግ አይደሉም፡፡ ዳኛም አይደሉም፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ጥፋተኛ ብለው ሊያውጁ አይገባም፡፡ ከተሰጣቸው ጭብጥ ውጭ ወጥተው ሊመሰክሩ አይገባም፡፡ ዳኛም አይደሉም፡፡ ዳኝነት እየሰጡ ነው፡፡ የሚያሳዝነው በዚች ምድር ስንት ጊዜ ልንኖር ነው? ፍርድ ቤቱ እየላላ (Lenient) እየሆነ ነው፡፡ የምናስደስተው ማንን ነው? ምስክሩ የሚያውቁትን እየመሰከሩ ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ ልጓም ሊያበጅላቸው እንደሚገባ በመግለጽ፣ ምስክሩን መቃወማቸውንና ምስክሩ በሐሰት ሊመሰክሩ እንደማይገባም መናገራቸውን ችሎቱ በትዕዛዙ ውስጥ አካቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ የጠበቆቹን ተቃውሞ በመቃወም፣ ለፍርድ ቤቱ የገለጸውን በሚመለከት ችሎቱ በትዕዛዙ እንዳሰፈረው፣ ምስክሩ የሚናገሩት ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው ፍትሕ ትልቅ ሚና አለው፡፡ የምስክሩ ማብራራት ለፍትሕ ስለሚጠቅም ነው፡፡ ጠበቃ ሕግን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ጠበቆቹ የችሎቱን ክብር በጠበቀ መልኩ መከራከር እንዳለባቸውና ምስክሩንም የችሎቱ አካል አድርገው ማየት እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ገልጿል፡፡ ጠበቆቹ ያደረጉት ነገር በጠበቆች ሥነ ምግባር ደንብም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ችሎቱ ተናግሯል፡፡

በምስክሩ ላይ በጠበቆቹ የተሰነዘሩት ፍሬ ነገሮች፣ ክብር የሚነኩ መሆናቸውንና ከሕግ ውጭ የተነሱ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማመኑን ገልጾ፣ ሁለቱም ጠበቆች ተመሳሳይ ድርጊት በፍፁም መድገም እንደሌለባቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ የትዕዛዙ ግልባጭ በፍትሕ ሚኒስቴር ለጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት እንዲደርሰው የሚለውን በልዩነት አስቀምጧል፡፡ የችሎቱ ዳኞች፣ ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋና ዳኛ በሪሁ ተወልደ ብርሃን ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ ዳኛ ጌታቸው ምትኩ በችሎቱና በጠበቆች መካከል ያለ ጉዳይ ወደ ሌላ አካል መተላለፍ እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ ጠበቆች በችሎት ሊገሰጹ እንደሚገባ ተናግረው፣ የተነገራቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በቂ በመሆኑ ለጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት መተላለፍ እንደሌለበት እምነታቸው መሆኑን በልዩነት አስፍረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን አሳውቆ እንደጨረሰ፣ የአቶ መላኩ ጠበቃ አቶ ተሻገር ለችሎቱ እንደገለጹት፣ ‹‹በችሎቱ ውስጥ የተናገርኩት ማንንም ለመጉዳት ወይም ማንንም ለመጥቀም አይደለም፡፡ እውነትን ለማፈላለግና ፍትሕን ለማገዝ ነው፡፡ ሦስተኛ ወገንንም ለመጉዳት አይደለም፤›› ካሉ በኋላ ፍርድ ቤቱንና አቶ እሸቱ ወልደ ሰማያትን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የፍርድ ቤቱን ሥራ የሚያስተጓጉሉ ከሆነና ሦስተኛ ወገንን የሚጐዱ ከሆነ፣ ደንበኛቸውን አቶ መላኩን አነጋግረው ጥብቅናቸውን እንዲያቆሙ ችሎቱን ጠየቁ፡፡

አቶ ተሻገር ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበው እንደጨረሱ አቶ መላኩ ተነስተው ለችሎቱ እንዳብራሩት፣ ጠበቃዬ ሲከራከሩ የገለጹበት ሁኔታ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ይኸም ትክክል ነው ፍርድ ቤቱ እንዳለው ሊታረም ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ጠበቃዬ በልበ ሙሉነት ይከራከራሉ ብዬ አላምንም፡፡ በእኔ በኩል ያስፈራኛል፡፡ በእኔ ምክንያት እንዲጐዱና የእኔ ዕጣ እንዲደርስባቸውም አልፈልግም፡፡ እኔ የማውቀውን ሀቅ እየነገርኳቸው ነው ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ የሚናገሩት፡፡ የማይናገሩ ከሆነ ደግሞ ጠበቆቻቸውን እንደሚያሰናብቱ፣ ተሸብረውና ተሳቅቀው እንዲከራከሩ እንደማይፈልጉ በመግለጽ፣ ጠበቆቻቸውን አሰናብተው በማረሚያ ቤት ሆነው ውሳኔ እንዲነገራቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ እንደገለጸው፣ ይቅርታውን እንደ መልካም ነገር ወስዷል፡፡ ቃላቶቹ መነገር እንደሌለባቸው ማመናቸውንም መቀበሉንና ሕግና ችሎትን ማክበር ትልቅነት መሆኑን አክሏል፡፡

ለትልቅ ሰው መገሰጽን መቀበል ትልቅነትን የሚያሳይ መሆኑን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ በማስጠንቀቂያ ማለፉ ከግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ የተከሳሹን መብት በሚያጠብ መልኩ ሊተረጐም እንደማይገባ ገልጾ፣ የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ የተሰጠው ጠበቆቹን ለማሸበርና ለማጨናነቅ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ ሕግና ሥርዓት ማክበር የጠበቆች ብቻ ሳይሆን የተከሳሾችም ጭምር መሆኑን የገለጸው ችሎቱ፣ በሌሎች መዝገብም ተመሳሳይ ትዕዛዝ መስጠቱን ገልጿል፡፡ ትዕዛዙ መብትን ለማጥበብ የታሰበ አይደለም፡፡ የችሎቱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባም አይደለም፡፡ ችሎቱ ሕግ ሲጣስ ግን ዝም ብሎ እንደማያይ ተናግሯል፡፡ አቶ መላኩ ‹‹የእኔ ዕጣ እንዲደርስባቸው አልፈልግም›› በማለት የሰጉት ሥጋት ግን የችሎቱ ሥጋት አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ ችሎቱ ከሕግ ውጪ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እንደሌለ፣ የትዕዛዙ ዓላማም ተከሳሽና ጠበቃ እንዲጨናነቁ አለመሆኑንና ሕግና ሥርዓት ማክበር ሁሉንም እንደሚጠቅም ገልጿል፡፡ የፍርድ ቤቱ ፍላጐት ውሳኔው በሕግና ማስረጃን መሠረት አድርጐ እንዲወሰን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መሆኑን አስረድቶ፣ ችሎቱ ፍትሕንና መብትን ለማረጋገጥ ጣልቃ እየገባ ጥያቄ እንደሚጠይቅም አሳውቋል፡፡ ትዕዛዙ የሚያሰጋና ሥራን የሚያስተው እንዳልሆነ አክሏል፡፡

የአቶ መላኩ ጠበቃ በድጋሚ ባቀረቡት ማመልከቻ ትዕዛዙ ለእሳቸው የሚሰጠው መልዕክት መኖሩን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ከአቶ መላኩ ጋር መቆየት እንደማይፈልጉ፣ ከእሳቸው ማረጋገጫ ይፈልጉ ስለነበርና እሳቸውም ለችሎቱ እንደገለጹ በማስታወስ፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከሚለው ትዕዛዝ በተጨማሪ ለፍትሕ ሚኒስቴር ይተላለፍ መባሉ ተገቢ አለመሆኑንና ሊያሠራቸው እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ስሜታዊ ሆነው የተናገሩ ቢሆንም ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችል ጉዳይ እንደሆነ የገለጹት ጠበቃ ተሻገር፣ አቶ እሸቱን ለመጉዳት ወይም አቶ መላኩን ለመጥቀም ሳይሆን ፍትሕ እንዳይጓደል ለማገዝ፣ እውነትን ለማውጣትና ነገ ፍርድ ቤት የነበሩ ዘመን ተቀይሮ የሚሆነው ስለማይታወቅ ትክክለኛ ውሳኔ ተሰጥቶ እንዲታለፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ወንድሞቼና አጐቶቼን ያጣሁበትን ሥርዓት የምጐዳ ከሆነ አልጠቅምም፤›› በማለት ንግግራቸውን አቁመዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጠበቃ ተሻገር እንዲረጋጉ ጠይቆ ‹‹ሁላችንም ስሜት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፤›› በማለት ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው ሥራ መልቀቅ አለባቸው ብሎ ችሎቱ እንደማያምን በድጋሚ ተናግሯል፡፡ በእውነት የሚይምኑ ከሆነም የፍትሕ ሥርዓቱን የማገዝ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ በማስጠንቀቂያ ሥራ አቋርጣለሁ ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑንም አክሏል፡፡ በመሆኑም ከደንበኛቸው ጋር በመመካከር እንዲያስቡበት መክሮ፣ ችሎቱ ግን እንደማያሰናብታቸው አሳውቋል፡፡ ስሜታቸው እንዲጐዳ እንደማይፈልግ፣ ከህሊናቸው ጋር እንዲማከሩና ለአቶ መላኩ መብት መጠበቅ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ ጭምርና ግራ ቀኙ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ችሎቱ አስረድቷል፡፡

አቶ ገብረዋህድ በበኩላቸው ባቀረቡት አቤቱታ፣ ዓቃቤ ሕግ ጭብጥ አስይዞ ምስክሩ የፈለጉትን ያህል እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ፣ ጠበቆች በመስቀለኛ ጥያቄ ያፈረሱትን የምስክርነት ቃል፣ ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ጥያቄ እየመራ ሊጠይቅ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ እሳቸው ያሉት ሳይሆን በሕግ የተከለከለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ጠበቃ ከመስቀለኛ ጥያቄ ውጪ ድጋሚ መጠየቅ ስለማይችል፣ ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ጥያቄ እየመራ ሲጠይቅ ፍርድ ቤቱ ሊያስቆም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ችሎቱ በማጣሪያ ጥያቄ እንዲጠይቅላቸው ቀደም ባሉ ምስክሮች ላይ ያቀረቡትን ጥያቄ እንዳለፈባቸው አቶ ገብረዋህድ አስታውሰው፣ በተያዘው ምስክርነት ላይ ዝም ብለው ማለፍ እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ምስክሩ ያልተካሄደን ስብሰባ እንደተካሄደ አድርገው መመስከራቸውን፣ ችሎቱ የሚያጣራው ይሆናል በሚል ተጠርጣሪዎች ሳይቃወሙ ቢያልፉና ፍርድ ቤቱ ሳያጣራ የውሳኔው አካል ቢያደርገው፣ እንደሚጐዱም አቶ ገብረዋህድ ጠቁመዋል፡፡ ጠበቃ እየመራ መስቀለኛ ጥያቄ ጠይቆ የሚፈልገውን ምላሽ ብቻ እንዲሰጠው እንጂ፣ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ ምስክሩ እንዲያብራራ መፍቀዱን እንደማይስማሙበት አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ጥያቄ መምራት እንደማይችል ተናግሯል፡፡ የአቶ መላኩና የጠበቃቸውም ጥያቄ ባለበት ታልፏል፡፡

No comments:

Post a Comment