Friday, December 26, 2014

ሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ከደቡብ ሱዳን መንግስት በቀረበባቸው ክስ ከሃላፊነት መነሳታቸው ታወቀ።

በደቡብ ሱዳን ለተሰማራው የተመድ የሰላም አስከባሪ ጦር አዛዥ የነበሩት ሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ከደቡብ ሱዳን መንግስት በቀረበባቸው ክስ ከሃላፊነት መነሳታቸው ታወቀ።

ህዳር 11 ቀን 2007 ዓም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን በአቤይ ግዛት ተሰማርቶ የነበረው የሰላም አስካባሪ ቡድን አዛዥ ሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል ተስፋማርያም በእ/ኤ/አ ጁን 19፣ 2014 ተልእኮዋቸውን ጨርሰው በሜ/ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገላልቻ መተካታቸውን ቢገልጽም፣ ኢሳት በዜና እወጃው አዛዡ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ መሰናበታቸውን ጠቅሶ ዘግቧል። የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደገለጹት ሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የተደረገው የደቡብ ሱዳን መንግስት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ መጻፉን ተከትሎ ነው።


የደቡብ ሱዳን መንግስት ጄ/ል ዮሃንስ ተግባራቸውን በብቃትና በገለልተኝነት ካለመምራታቸውም በላይ በኦጋዴን የሰራዊት አዛዥ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት፣ በሶማሊ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም የሚጠረጠሩ መሆናቸውን አያይዞ ጠቅሷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም አፋጣኝ ውሳኔ በመስጠት ጄኔራሉ እንዲተኩ ማደረጉን ምንጮች ገልጸዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት የአዲስ አበባው አስተዳደር በያዘው አቋም ደስተኛ ካለመሆኑም በተጨማሪ የተቃዋሚውን መሪ ሪክ ማቻርን በጋምቤላ በኩል እያስታጠቀ ነው በሚል ወቀሳ እያቀረበ ነው። በቅርቡ አዲስ አበባ ነበሩት ፐ/ት ሳልቫኪር በግድ የቀረበላቸውን የሰላም ስምምነት አልፈርምም በማለታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይጓዙ አስተጓጉለዋቸው እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። የኢህአዴግ መንግስት ለሳልቫኪር አውሮፕላን በመላክ አዲስ አበባ ድረስ ካስመጣቸው በሁዋላ፣ ፕ/ቱ የሰላም ስምምነቱን አምኜበት እንጅ በግፊት አልፈርምም በማለት ወደ አገራቸው ለመመለስ ሙከራ ሲያደርጉ አውሮፕላን የለም በመባላቸው በጣም ተበሳጭተው እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት የኢህአዴግ መንግስት በፌደራል ደረጃ ገለልተኛ መስሎ ይቀርባል፣ በጋምቤላ ክልል በኩል ደግሞ የሪክ ማቻርን ሰራዊት ከማስታጠቅ ጀምሮ ለቁስለኞች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ነው በማለት ይከሳል። በተለይም የኢህአዴግ መንግስት በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም በደቡብ ሱዳን ውስጥም ተግባራዊ እንዲሆን የሚያደርገው ሩጫ በሳልቫኪር በኩል ተቀባይነት አላገኘም።
የሳልቫኪር መንግስት በጁባ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የህወሃት የቀድሞ የጦር አባሎች በሙሉ ከአገሪቱ ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ላይ ነው።

በጦር አማካሪነት ይሰሩ የነበሩትም በተመሳሳይ መልኩ ተቀንሰዋል። ኡጋንዳ ጦሯን ወደ ጁባ በመላክ ቀድሞ በህወሃት የቀድሞ ጄኔራሎች ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን ተክታ በመስራት ላይ ናት። ድርጊቱ ያበሳጨው ኢህአዴግ የኡጋንዳ ጦር ከአገሪቱ ለቆ እንዲወጣ ቢወተውትም እስካሁን አልተሳካለትም፤ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም በተፋላሚ ወገኖች ላይ ማእቀብ ይጣላል በማለት እያስጠነቀቁ ነው። ይሁን እንጅ ቻይና ነዳጅ የማውጣት እንቅስቃሴ በመጀመሩዋ፣ የሳልቫኪርን መንግስት በማእቀብ ለማንበረከክ የመቻሉ እድል የመነመነ ነው የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ከደቡብ ሱዳን የሚፈልሱትን ዜጎች በተመለከተ በጋምቤላ ክልል ባለስልጣናትና በፌደራል መንግስት መካከል ልዩነት ተፈጥሯል። የአዲስ አበባው የኢህአዴግ መንግስት ከደቡብ ሱዳን የሚፈልሱ የኑዌር ተወላጆች በክልሉ ብቻ እንዲሰፍሩ በማድረግ ያለውን የህዝብ ቁጥር ሚዛን እንዲዛባ እያደረጉ ነው በማለት የክልሉ ባለስልጣናት ወቀሳ ከማቅረባቸውም በላይ የሚሰደዱት ደቡብ ሱዳናውያን በሁሉም ክልሎች በእኩል ደረጃ ተበታትነው እንዲሰፍሩ በመጠየቅ ላይ ናቸው። ይሁን እንጅ የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናት የሚያቀርቡት ጥያቄ በአዲስ አበባው መንግስት በኩል ተቀባይነት አላገኘም።


No comments:

Post a Comment