Tuesday, December 30, 2014

በኮምቦልቻ የገዢውን ፓርቲ ካድሬዎች በጥያቄ ያፋጣጡ ተማሪዎች ህዝብ ልታሳምጹ ነው የሚል ማስጠንቀቂያዎች ደረሳቸው

ታኀሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው እሮብ ጀምሮ ለ3 ቀናት በተካሄደው የመሰናዶና የመምህራን የፖለቲካ ስልጠና ላይ የገዚውን ፓርቲ ካድሬዎች በጥያቄ ከማፋጠጥ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ በሚታየው ዘረኝነት፣ የፍትህ እጦትና ሙስና ላይ አስተያየቶችን የሰጡ ተማሪዎች ከስብሰባው መጠናቀቅ በሁዋላ ተማሪውንና ህዝቡን ለአመጽ ለማነሳሳት አስባችሁዋል በሚል ማስጠንቀቂያና ባስፈራሪያ እንደደረሳቸው ዘጋቢያችን ገልጻለች።ለተማሪዎች በሚሊኒየም ትምህርት ቤት በፕላዝማ የተደገፈ የ3 ቀናት ስልጠና ሲሰጥ፣ ለመምህራን ደግሞ በቢራሮ አዳራሽ ለ4 ቀናት የቆየ ስልጠና ተሰጥቷል። መድረኩን የሚመሩት ባለስልጣን በውጭ አገር የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛ መረጃ አያሰራጩም በማለት መናገራቸውን ተከትሎ  ተማሪዎች በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች ከኢቲቪ ቀድመው መረጃ በመናገር ተአማኒነትን ማትረፋቸውን ለዚህም ደግሞ በየጊዜው የሚከዱ ባለስልጣናት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አቶ በረከት ስምኦን የሂትለር የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ፣ ውሸት ሲደጋጋም እውነት ይሆናል ያሉትን በተደጋጋሚ እንደሚናገሩና፣ ይህንኑ በኢቲቪ ላይ ተግባራዊ እያደረጉት መሆኑን ተማሪዎች ተናግረዋል።የመለስ ዜናዊን ማረፍ መጀመሪያ የሰማነው ከውጭ ሚዲያዎች ነው፣ ኢቲቪ ዜናውን የነገረን ከ2 ወር በሁዋላ ዘገይቶ በማለት በውጭ ሚዲያዎችን ላይ የቀረበውን ትችት ተከላክለዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በየጊዜው መክዳታቸው መረጃ ለማግኘት አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት ተማሪዎች፣ ኢሳት በጋዜጠኛ አበበ ቶላ ወይም አቤ ቶክቻው አማካኝነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞችን ህብረት ፕሬዚዳንትን ቃለ ምልልስ በማድረግ ያቀረበው ዘገባ፣ የመንግስት ባለስልጣናት እውነተኛ ፍላጎት የሚያሳይ ነው ሲሉ አክለዋል።በጋምቤላ በመዠንገር አካባቢ የደረሱ ጭፍጨፋዎችንና ሌሎችንም በርካታ የአገራችን ችግሮች የሰማነው በውጭ ሚዲያው በመሆኑ፣ በሚዲያው ላይ የሚቀርበው ወቀሳ ትክክል አይደለም ብለዋል።የብሄር ግጭትን በተመለከተ ዋናው ተጠያቂው መንግስት ነው ያሉት ተማሪዎች፣ በተለይ የትግራይን ህዝብ ከአማራውና ከኦሮሞው ጋር ለማጋጨት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሁዋላ ላይ አገሪቱን ይጎዳታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ተማሪዎች ካነሱዋቸው ቅሬታዎች መካከል አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በስልጤ ወራቢ ተገኝተው ስለተናገሩት እና በቀይ ባህር ላይ ስላለቁት ኢትዮጵያውያን ይገኝበታል። አንድ ጠ/ሚኒስትር እንዴት የገዛ ዜጎችን ገረድ ብሎ ይሳደባል ሲሉ የጠየቁት ተማሪዎች፣ እንዲህ አይነት ንግግር እንኳንስ አገር ከሚመራ ከተራ ዜጋም አይጠበቅም በማለት ተችተዋል። መንግስት ለመለስ ዜናዊ  ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት በስርአት እንዲቀበሩ ማድረጉን ያስታወሱት ተማሪዎች፣ በቅርቡ ወደ የመን ሲሄዱ ላለቁ ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን ሌላው ቢቀር  ሰንደቃላማ እንኳን ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አለመደረጉ በዜጎች መካከል ያለውን ልዩነት የሚየሳይ ነው በማለት አክለዋል።የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ በአገራችን ፍትህ እንደሌለ የሚያሳይ ነው በማለት የፍትህ ስርአቱን የተቹት የመሰናዶ ተማሪዎች፣ አቶ አንዳርጋቸው ከስድስት ወራት የእስር ጊዜ በሁዋላ፣ በቤተሰብና በጠበቃ እንዳይጎበኙ፣ የታሰሩበትም እንዳይታወቅ መደረጉ የፍትህ ስርአቱ በአገራችን መቀበሩን ያሳያል ብለዋል።የመንግስት ባለስልጣናት እየጠፉ መሆናቸው ስርአቱ የገባበትን ችግር ያሳያል የሚሉት ተማሪዎች፣ ከዚህ ቀደም አቶ ኤርምያስ ለገሰ ስርአቱን ጥለው በመጥፋት በሙስና በኩል የሚታየውን ችግር ማጋለጣቸውን አውስተዋል። ሰሞኑን 3 የአየር ሃይል አባላት ሄሊኮፕተር ይዘው መሰወራቸው መንግስት ያለበትን ችግር እንደሚያሳይ ተማሪዎች ተናግረዋል።አንዳንድ ተማሪዎች የአገራችን ችግር እንደ ባሉን እየተወጠረ በመሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በጊዜ መፍትሄ ካልተፈለገለት እንደ ሊቢያና ኢራቅ ልንሆን እንችላለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ተማሪዎች ስብሰባው በመካሄዱ ድስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ስብሰባው ከመረጃ ሩቅ የነበሩ ሰዎች ጥያቄዎችን እንዲያነሱ መርዳቱን፣ በየቀኑ ይታይ የነበረው ክርክርና ፍጥጫ ሌሎች ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረጉን፣ ተሳታፊዎች ብሶታቸውን እንዲተነፍሱ ማስቻሉን፣ በአጠቃላይ ወጣቱ ለለውጥ መነሳቱን ለማየት የቻልንበት መድረክ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱ ጠቀመን እንጅ አልጎዳንም ብለዋል።

No comments:

Post a Comment