Friday, September 28, 2018

በብአዴን ጉባኤ ላይ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አልተገኙም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 18/2011) በባህርዳር እየተካሄደ ባለው የብአዴን ጉባኤ የለውጥ አደናቃፊ የሚባሉት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አልተገኙም ተባለ።
በጉባኤው ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን ጨምሮ ብአዴንን ሲያሽከረክሩት የነበሩት አንጋፍዎቹ የአመራር አባላት አለመገኘታቸው ታውቋል።በ12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ አልተገኙም ከተባሉት አባላት መካከልም አቶ ከበደ ጫኔና አቶ አዲሱ ለገሰ ይገኙበታል።
የብአዴንን ጉባኤ በፕሬዝዲየም አባልነት ኣንዲመሩ የተመረጡት አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ዶክተር አምባቸው መኮንን፣አቶ ብናልፍ አንዱአለምና አቶ ምግባሩ ከበደ ናቸው።

አቶ በረከት ስምኦን ከባህርዳሩ ጉባኤ ሰሽተው በመቀሌ የመስቀልን በአል ከሕወሃቶች ጋር ሲያከብሩ ታይተዋል።
በብአዴን ጉባኤ ለውጥ ያደናቅፋሉ የተባሉት አቶ ጌታቸው አምባዬ፣አቶ ከበደ ጫኔ፣አቶ አህመድ አብተው፣ወይዘሮ ዝማም ከበደና ሌሎች ተወግደው በወጣት አመራሮች ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የብአዴን ጉባኤ ትላንት በባህርዳር ሲጀመር የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንንና ምክትላቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለለውጡ ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽ ከዘበኝነት ወተናል ማለታቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment