Tuesday, September 18, 2018

አቶ ኦባንግ ሜቶ አቀባበል ተደረገላቸው

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 8/2011)የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በጋምቤላ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።
አቶ ኦባንግ ሜቶ ከ16 ዓመታት በኋላ ወደ ጋምቤላ ሲያመሩ የከተማዋ ነዋሪዎችና የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት አደባባይ በመውጣት እንደተቀበሏቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አቶ ኦባንግ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የልዑካን ቡድን አባላትን በመምራት ወደ ኢትዮጵያ ያመሩት ከአንድ ሳምንት በፊት ሲሆን ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ስማቸው ከሚጠቀሱ የሰብዓዊ መብት ታጋዮች ግንባር ቀደም ናቸው።
በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን ስቃይና መከራ ሲደርስባቸው ድምጻቸውን ከማሰማት አንስቶ ቦታው ድረስ በመሄድ ከወገናቸው ጎን በመቆም ከመንግስታት ጋር ሆነው የሚሟገቱ፡ ለኢትዮጵያውያን ጠበቃ ሆነው የሚቆሙ ሰው ናቸው- አቶ ኦባንግ ሜቶ።

ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ያቋቋሙት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ሀገራዊ ተግባራትን ሲያከናወን መቆየቱ የሚታወቅ ነው።
አቶ ኦባንግ ሜቶ የኢትዮጵያውያን አምባሳደር በመሆን ከሀገር ሀገር ተንቀሳቅሰዋል።
ከሃያላን መንግስታት ተወካዮች ጋር እየተገናኙ በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አጠቃላይ ጭቆና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲታወቅ በማድረግ በርካታ ሰራዎችን አከናውነዋል።
የአኝዋክ ተወላጅ የሆኑት አቶ ኦባንግ በብሄር ፖለቲካ በተከፋፈለው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ የአንድነት ሃይሉ ምልክት በመሆን በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘት አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶ ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያ የነበሩት በአኝዋኮች የጭፍጨፋ ወቅት ነበር።
በጊዜው በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ከ400 በላይ የአኝዋክ ተወላጆች በአንድ ቀን በተገደሉ ጊዜ አቶ ኦባንግ ወደ ሰሜን አሜሪካ መጥተዋል።
ከዚያን ወዲህ ነው ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ ሊሆን አይችልም የሚል መሪ ቃል ይዘው በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ትግላቸውን ያጠናከሩት።
በዚህን ወቅትም በህወሀት አገዛዝ ሽብርተኛ ተብለው በሌሉበት የ15 ዓምታት እስር ተላልፎባቸዋል።
ከ16 ዓመታት ነሀሴ 30 2010 ዓመተ ምህረት ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አመራር አባላት ጋር በመሆን ወደ ሀገር ቤት የገቡት አቶ ኦባንግ ሜቶ ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
በትውልድ አከባቢያቸው ጋምቤላ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል ደማቅ መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች በ20 ዓመታት የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴያቸው ላበረከቱት ሀገራዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ክብር ተሰጥቶአቸዋል።
የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ በሞተር ሳይክልና በተለያዩ ተሽከርካሪዎች በማጀብ በጋምቤላ ከተማ አውራጎዳናዎች እየተዘዋሩ ለነበሩት ለአቶ ኦባንግ ሜቶ ያለውን ክብር አሳይቷል።

No comments:

Post a Comment