Wednesday, September 26, 2018

የአየር ትራፊክ ሰራተኞች ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነ።

ፍርድ ቤቱ በዋስ እንዲወጡ ትላንት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን አቃቢ ሕግ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ እጠይቃለሁ ማለቱ ተመልክቷል።

በሃገሪቱ ላይ የ70 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ኪሳራ አድርሰዋል በሚል ተጠርጥረው የአየር ትራፊክ ተቆጣጠሪ ሰራተኞች በ20ሺ ብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ የወሰነው ትላንት ነው።


ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የአየር ትራፊክ ሰራተኞች ከእስር ቤት ስለመውጣታቸው የታወቀ ነገር የለም።

አቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ተቀባይነት ካገኘ ዋስትናው ሊታገድና እስረኞቹም በወህኒ ሊቆዩ እንደሚችሉ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ነሐሴ 21 ቀን 2010 አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ አስተባባሪ የተባሉ 9 ሰዎች ታስረዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን በአድማው ወቅት የውጭ ዜጎችንና ጡረተኞችን በማሳተፍ ስራ እንዳይስተጓጎል ማድረጉ ይታወሳል።

ሆኖም ከጡረተኞቹና የውጭ ዜጋ ከሆኑት የኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር መናበብ አልቻልንም በሚል የኬንያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር የተቃውሞ ድምጹን ማሰማቱም አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የኬንያውያኑን ውንጀላ በወቅቱ ውድቅ አድርጎታል።

ነሐሴ 30 ቀን 2010 አመተ ምህረት ከጆሃንስበርግ ወደ አዲስ አበባ የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንና ወደ ዛንዚባር ይጓዝ የነበረው የጣሊያን አውሮፕላን በኬንያ የአየር ክልል በተመሳሳይ ከፍታ ላይ ሲበሩ ከባድ ከሚባል አደጋ ለጥቂት መትረፋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment