Thursday, September 27, 2018

“አዲሱ አስተሳሰብ አሮጌውን ያሸንፋል” ሲሉ የብአዴን ሊቀመንበር ተናገሩ

( ኢሳት ዜና መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ/ም ) ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር አሁን የሚታየው ግጭት በአሮጌው አስተሳሰብ እና በአዲስ አስተሳሰብ መካከል በሚፈጠር ቅራኔ የመጣ ነው። አዲሱ አስተሳሰብ አሮጌውን ያሸንፋል ሲሉም በእርግጠኝነት ተናግረዋል። አቶ ደመቀ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ከመወጋገዝ ይለቅ መተጋገዝ፣ ከመጠላለፍ ይለቅ መተቃቀፍ እንዲሁም ከመሰባበር ይልቅ መተባበር እንደሚገባ ገልጸዋል። ለውጡ በብርቱ ትግል የመጣ እንደመሆኑ፣ ለውጡን ለማስቀጠልም ብርቱ ትግል ይጠይቃል ብለዋል። አገሪቱ በሁለት የፖለቲካ አስተሳሰቦች መካከል እየተናጠች እንደምትገኝ የገለጹት አቶ ደመቀ፣ በአንድ በኩል አህዳዊ አስተሳሰብን ለማስፈን የሚፈልጉ በሌላ በኩል ደግሞ ብሄረሰባዊ ማንነትን ከሌሎች ለመነጠል የሚሹ ሃይሎች በሁለት ጫፍ ቆመው እየታገሉ ነው ። የድርጅቱ ምክትል ሊ/መንበርና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ዘመኑ እርስ በርስ የምንወነጃጀልበት ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር የምንጓዝበት ነው ብለዋል። በክልሉ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን የገለጹት አቶ ገዱ፣ በክልሉ ስራ መፍጠር ዋናው ፈተና ሆኗል ብለዋል። የጨለማው ዘመን ምዕራፍ እስከወዲያኛው መዘጋቱንና አዲስ የተስፋ ጸዳል እየመጣ ቢሆንም፣ ለውጡ ቀጣይነት የሚኖረው ተቋማት ሲገነቡ ነው በማለት ድርጅታቸው ለተቋማት ግንባታ ተገቢውን ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል። በዚህ ጉባኤ ወጣቶች ወደ አመራር ቦታ እንዲመጡ መደረግ እንዳለበት ሁለቱም የብአዴን መሪዎች አሳስበዋል።

No comments:

Post a Comment