Friday, September 14, 2018

የሕወሃት ደጋፊዎች በግልጽ ቅስቀሳ ጀመሩ

(ኢሳት ዲሲ--መስከረም 4/2011) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የኦነግ ልኡካንን ለመቀበል የሚደረገው ዝግጅት ወደ ግጭት እንዲያመራ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ደጋፊዎች በግልጽ ቅስቀሳ መጀመራቸው ታወቀ።

ጸረ ለውጥ ሃይሎች የሚያደርጉትን ይህንን እንቅስቃሴ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች በቅንጅት እንዲያከሽፉትም ጥሪ ቀርቧል።

ወደ ሃገራቸው የሚገቡት የኦነግ ልኡካን አቀባበል ሰላማዊና ደማቅ ሆኖ በስነስርአት እንዲጠናቀቅ ሁለቱም ወገኖች በመቻቻልና በመግባባት እንዲንቀሳቀሱ፣የፖለቲካ መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
በአርማና በሰንደቅ አላማ የተፈጠረው ውዝግብ ከትልቁ ስዕል ያወጣናል ሲሉም አሳስበዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ አክራሪ ሃይሎች አጋጣሚውን በመጠቀም፣ግጭት ለመፍጠርና ለማባባስ፣በመንግስት ተቋማት እንዲሁም በታሪካዊ ሃውልቶችና መሰል ቦታዎች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር በቅንጅት ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም እየተከሰተ ያለውን ሁኔታ በተመለከተም አቶ ለማ መገርሳ ለወጣቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕዝብ የፈለገውን ሰንደቅ አላማና አርማ እንዲይዝ መፍቀድ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን ያሰፋዋል ሲሉ አቶ ለማ መገርሳ ገልጸዋል።
በሰንደቅ አላማና በአርማ ሳቢያ ግጭት ውስጥ መግባት አስፈላጊ አይደለም በማለት የተናገሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ማንም የራሱን ሰንደቅ አላማና አርማ ይዞ ቢወጣ ወንጀል አይደለም ብለዋል።
በዚህም ሳቢያ ሰላምና እድገትን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ወደ ኋላ ሊመለስ እንደማይገባው አስገንዝበዋል።
“በሰንደቅ አላማ ምክንያት አላስፈላጊ እልህ ውስጥ ገብተን ወደ ኋላ ሊመልሱን ለሚፈልጉ ወገኖች መንገድ መክፈት የለብንም ሲሉም አቶ ለማ አሳሰበዋል።
ከሁሉም ወገን ትዕግስት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ለማ መገርሳ የፖለቲካ ድርጅቶችና ወጣቶችም በዚህ ረገድ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠየቀዋል።

No comments:

Post a Comment