Monday, September 17, 2018

በቡራዩና አካባቢው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ25 ይበልጣል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 7/2011)በቡራዩ፣በአሸዋ ሜዳና በከታ በሳምንቱ መጨረሻ በንጹሃን ላይ በደረሰው ጥቃት
ከ25 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ይህንን ጥቃት ለመቃወም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከወጡ ዜጎች መካከልም 5 ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ግድያውም መሳሪያ በነጠቁ ግለሰቦች ላይ የተፈጸመ ነው ብሏል።


በቡራዩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ዜጎች ቁጥራቸው የበዛ መሆኑንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ በቡራዩ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ25 በላይ መሆኑን ገልጸው ትክክለኛውን ቁጥር አጣርተን እንገልጻለን ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውም ታውቋል።
በቡራዩ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ አዲስ አበባ ላይ ለተቃውሞ የወጡት ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን በሰላም አሰምተው በሰላም መመለሳቸውንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የተወሰኑ በቡድን የተደራጁ ወገኖች ግን ችግር የማባባስ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ሃይሎች ቦምብ ይዘው መገኘታቸውንና ከጸጥታ ሃይሉ ላይ መሳሪያ መንጠቃቸውንም አመልክተዋል።

በዚህም ከጸጥታ ሃይሉ በተሰጠ የአጸፋ ምላሽ 5 ሰዎች መገደላቸውንና የቆሰሉ መኖራቸውንም አመልክተዋል።
በቡራዩ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ በአርባምንጭም ሰልፍ መካሄዱ ታዉቋል።

No comments:

Post a Comment