Friday, September 21, 2018

ኢትዮጵያ የተደቀኑባት ፈተናዎች የገዘፉ መሆናቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 11/2011) ኢትዮጵያ የተደቀኑባት ፈተናዎች የገዘፉ መሆናቸውን አቶ ሌንጮ ለታ ገለጹ።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ የፖለቲካ ሃይሎችም ከችግሩ ስፋት አንጻር በሃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሶቹ የኢሕአዴግ መሪዎች ከ27ቱ አመት ኢሕአዴግ በተለየ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/በቅርቡ በቀጣይ ጉዞው ላይ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍም አስታውቀዋል። ለዊሊያም ዴቪሰን በኢትዮ-ኢንሳይት ላይ ቃለ ምልልስ የሰጡት አቶ ሌንጮ ለታ ለፖለቲካ ሃይሎችም ምክር ለግሰዋል።
ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ማምጣት ይቻላልን በማለት ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሌንጮ ለታ “የትኛው ኢሕአዴግ” በማለት ምላሽእቸውን የጀመሩት አቶ ሌንጮ ለታ በሃገሪቱ የማሻሻያ ርምጃዎችን እየወሰደ ያለው ኢሕአዴግ፣አምና ከነበረው ኢሕአዴግ በመሰረቱ ፍጹም የተለየ ነው ብለዋል። 

ያነጋገሯቸው የመንግስት ባለስልጣናት ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት እንዲሁም ወታደራዊና የጸጥታ መዋቅሮችን ከፖለቲካው ውጪ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን መረዳታቸውን ገልጸዋል። ከዚህም በመነሳት ላለፉት 27 አመታት ከነበረው ኢሕአዴግ ጋር ሳይሆን ከሌለ ኢሕአዴግ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የኢሕአዴግ መሰነጣጠቅ በሃገሪቱ መረጋጋት ላይ ተጽእኖ ያመጣል የሚል ስጋት አለዎት ወይ በሚል የተጠየቁት አቶ ሌንጮ ለታ የሚያሳስቧቸው በርካታ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል። ትኩረት ያልተሰጠው የሕዝብ ቁጥር እድገት በአጭር ጊዜ ካልተገታ አሳሳቢ ሁኔታ እንደሚደቅን ገልጸዋል። ሃገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁኔታም እንደሚያሳስባቸው የገለጹት አቶ ሌንጮ ለታ ሃገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ከፍተኛ የጥንቃቄ ጉዞ እንዲያደርጉም መክረዋል።
ስለ ድርጅታቸው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ኦዴግና ስለራሳቸው ቀጣይ እቅድ የተጠየቁት አቶ ሌንጮ ለታ በቅርቡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በዚህም በሃገሪቱ ሕግ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲሁም ከሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የመዋሃድ ወይንም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን ቁጥር ለመቀነስ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment