Wednesday, September 19, 2018

ኢትዮጵያና ኤርትራ የተፈራረሙት ባለ ሰባት አንቀጽ ስምምነት ይፋ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 9/2011) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ የተፈራረሙት ባለ ሰባት አንቀጽ ስምምነት ይፋ ሆነ።
ባለፈው ሳምንት በሳውዳረቢያ ጅዳ ሁለቱ መሪዎች በፈረሙት ስምምነት መሰረት በጸጥታና መከላከያ እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።
በባህልና በማህበራዊ ጉዳዮች ጭምር በትብብር ለመስራት ፊርማቸውን ያኖሩት ሁለቱ መሪዎች በጋራ ኢንቨስትመንት ለመሰማራትና የጋራ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለመፍጠር መስማማታቸው ተመልክቷል።
የጦርነቱ ዘመን አክትሞ የሰላም ዘመን መግባቱን፣ወዳጅነትና አጠቃላይ ትብብር መጀመሩን በአንቀጽ አንድ ላይ ያስቀመጠው የሁለቱ መንግስታት የስምምነት ሰነድ፣በጸጥታና መከላከያ፣በንግድና ኢንቨስትመንትና በሌሎችም መስኮች በትብብርና በቅንጅት ለመስራት መስማማታቸውን ይዘረዝራል።
የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ዘሔግ ኔዘርላንድ ከ15 አመታት በፊት ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ በዚሁ ስምምነት ላይ ጭምር ያረጋገጡት ሁለቱ መሪዎች ለአካባቢውና ለአለም ሰላምና ጸጥታ ለመስራት እንዲሁም ሽብርን ለመዋጋት እንዲሁም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የመሳሪያና የአንደንዛዥ እጾችን ዝውውር ለመግታትም ተስማምተዋል።

ይህም አለም አቀፍ ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሆነም ተመልክቷል።
በሁለቱ መሪዎች ደረጃ የተፈረመውን ስምምነት አፈጻጸሙን የሚከታተልና የሚመራ አብይና ንኡስ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተዋል።
በአማርኛ፣በትግርኛ፣በአረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ይህ ስምምነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 16/2018 ጅዳ ሳውዳረቢያ ላይ ተፈርሟል።
በትርጓሜ ላይ የሚፈጠር ችግር ቢገጥም የእንግሊዝኛው ቅጂ በዋና ሰነድነት እንዲያዝም ተስማምተዋል።
ሁለቱ መሪዎች ስምምነቱን ባደረጉበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣የሳውዲው ንጉስና አልጋወራሽ ልኡል መሃመድ ሰልማን ተገኝተዋል።
ለሁለቱም መሪዎች ላመጡት ሰላም የሳውዲ ከፍተኛ ሜዳሊያም ተሸልመዋል።

No comments:

Post a Comment