Wednesday, September 19, 2018

ኢትዮጵያን ከመገንባቱ ሂደት ማንም ሃይል ሊያስቆመን አይችልም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 9/2011) ኢትዮጵያን ከመገንባቱ ሂደት ማንም ሃይል ሊያስቆመን አይችልም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
ኢትዮጵያንም አፍሪካንም እንገነባለን ያሉት ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህልውና እንዲቀጥል ኦሮሞዎች ሃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በጅማ ዛሬ በተጀመረው የኦህዴድ 9ኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦህዴድ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጠላት ጋር ሆናችሁ የኦሮሞን ትግል ወደኋላ ለመመለስ ያሰባችሁ ካላችሁ ከጠላት ለይተን አናያችሁም ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ኢትዮጵያ ከጠላቶቿ ጋር ባደረገችው ጦርነት ሁሉ ኦሮሞዎች ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የዚህች ሐገር አንድነት ለማስጠበቅም ኦሮሞዎች ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በጅማ ዛሬ በተጀመረው የኦሕዴድ ጉባኤ ላይ ጅማን መሰረት አድርገው የጅማውን አባጅፋር የጠቀሱት ዶ/ር አብይ አህመድ አባጅፋር ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ጭምር አርቀው የሚያስቡ ነበሩ ሲሉ ምስክርነት ሰጥተዋል።

ከዚህ በኋላ በኦሮሞ ስም መነገድ አይቻልም በማለት መልዕክት ያስተላለፉት ዶክተር አብይ አህመድ አብሮ መቆም ማለት ጠዋት እዚህ እዚያ መገኝት አይደለም በማለት አሳስበዋል።
የህግ የበላይነት የማስከብር ሃላፊነታችንን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ሲሉም ሕግና ስርዓትን ለማስከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ከመገንባት ምንም ሃይል ሊያስቆመን አይችልም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንትና የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ለሐገራችን ሰላምና አንድነት ተባብረን በጋራ መስራት ይገባናል ብለዋል።
መብታችንን ማስጠበቅ እንዳለብን ሁሉ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ የሌሎች ማህበረሰብ መብቶች መጠበቅ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

No comments:

Post a Comment