Thursday, November 2, 2017

የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ መሪዎች በሜቴክ የተገነባውን ፋብሪካው እንደማይረከቡ ታወቀ

የፋብሪካው የአመራር አካላት ፋብሪካውን እንደማይረከቡ ያስታወቁት ግንባታው ጥራት የለውም በሚል ምክንያት ነው።
በህወሃት የሚደገፉ የመገናኛ ብዙሃን የኦሞ ኩራዝ 1 የስኳር ፋብሪካ ስራ መጀመሩን እና ፋብሪካው በቀን 650 ቶን ስኳር እንደሚያመርት፣ በተጓዳኝም ከፋብሪካው በሚገኝ ተረፈ ምርት ከፋብሪካው ተርፎ ለሌላ የሚተላለፍ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ፣ በቀጣይም ምርቱን በእጥፍ አሳድጎ እስከ 1.3 ሺህ ወይም 1 ሽህ 300 ቶን ስኳር በየቀኑ እንደሚያመርት ገልጸው ነበር።
የፋብሪካው ሰራተኞች በበኩላቸው የአገርና የሕዝብ ገንዘብ ፈሶበት ለዓመታት እየተጓተተ ለከፍተኛ ምዝበራ የተጋለጠውን ድርጅታቸውን አስመልክቶ እየተሰጡ ያሉት መረጃዎች ከእውነታው የራቁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
‹‹ሜቴክ ለፕሮጀክት ጽ/ቤቱ እንኳን ደስ ያላችሁ፣ ፋብሪካችሁን ምርት አስጀምረናልና ተቀበሉን ›› የሚል ደብዳቤ መጻፉን የሚናገሩት የፋብሪካው ሰራተኞች ፣ ስራ አመራሩ ግን ፣ ''ስለ ፋብሪካው የኤሌክትሪክ ሥርዓት፣ የተለያዩ ማምረቻ ክፍሎች መቀናበር፣ የሜካኒካል ክፍሎች በትክክል ለሥራ መዘጋጀታቸውን በአጠቃላይም ፋብሪካው ትክክለኛ ምርት ለማምረት ብቁ መሆኑን በባለሙያ ሳናረጋግጥ አንቀበልም። ያየነው የተጠናቀቀ ምርት የለም።'' በሚል ፋብሪካውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት በፕሮጀክቱ የሥራ አመራር አባላት ላይ በሜቴክ የጦር ሹማምንት ማስፈራሪያና ዛቻ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። ኃላፊዎቹ በዚሁ ሰግተውና ስለ ጉዳዩ ለማስረዳት ሥራ አስኪያጁ የተወሰኑ የሥራ መሪዎች ጋር አዲስ አበባ ስኳር ኮርፖሬሽን መሥሪያ ቤት መሄዳቸውንና እዚያ እንደሚገኙም ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ የሄደው የአስተዳደር ቡድን ጉዳዩን ለኮርፖሬሽኑ አስረድቶ ላለመቀበል ያቀረበው ምክንያት በስኳር ኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ተቀባይነት አግኝቷል። ጉዳዩን በጋራ ለኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ማቅረባቸውንና በቦርዱ ሰብሳቢም ተቀባይነት አግኝቶ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ በቅርብ ውሳኔ ያገኛል በመባላቸው አዲስ አበባ ሆነው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሜቴክ ይህን ፕሮጀክት በሚመለከት ባቀረበው ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጭምር ማሳሳቱንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአንድና ሁለት ወር ወደ ማምረት ይገባል ካሉ ጊዜ ጀምሮ ፋብሪካው ምንም ስራ ሳይጀምር ስድስት ወራት ማለፉን ምንጮች ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከኩራዝ 1 ፕሮጀክት ከዓመታት በኋላ የተጀመረውና በቻይናዎች የሚገነባው የኦሞ ኩራዝ 2 ፕሮጀክት የፋብሪካ ተከላ ተጠናቆ በሙከራ ምርት ትክክለኛ ስኳር ያመረተ ቢሆንም፣ የሜቴክ ባለስልጣናት “እኛን ያስወቅሳል” የሚል ምክንያት በማቅረብ ወደ ምርት እንዳይገባ አግደዋል። ፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ከፕሮጀክት 1 እንዳያገኝ በማድረግ ተጽዕኖ በማሳደር እንዲሁም በፕሮጀክቱ ማሳ ለምርት የደረሰ ሸንኮራ ባለመኖሩ በቅርብ ሊጀምር እንደማይችል፣ ይህም በስኳር ፕሮጀክቶች ያለውን የዕቅድ ክፍተት ያመለክታል ሲሉ ምንጮቻችን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ሰአት በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የስኳር እጥረት በመፈጠሩ በውድ ዋጋ እየተቸበቸበ ነው። በቅርቡ በድብቅ ወደ ኬንያ ሊላክ የነበረ 44 ሺ ኩንታል ስኳር ኢሳት መረጃውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ወደ ወንጂ ፋብሪካ እንዲመለስ መደረጉ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment