Monday, November 27, 2017

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነው ዮናታን ተስፋዬ 3 አመት ከመንፈቅ ተፈረደበት

(ኢሳት ዜና ህዳር 18 ቀን 2010 ዓም)
ወጣት ዮናታን ቀደም ብሎ በሽብር ወንጀል ተከሶ 6 ዓመት ከመንፈቅ ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የሽብር ወንጀል ክሱ ወደ መደበኛ ወንጀል ተለውጦ 3 ዓመት ከመንፈቅ እንዲታሰር ተፈርዶበታል።
ወጣት ዮናታን በፌስቡክ ገጹ ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎች የተነሳ መከሰሱ ይታወቃል። ዮናታን አመክሮ ከተሰጠው ከአምስት ወራት እስር በሁዋላ ሊፈታ ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ በእነ ክንዱ ዱቤ ክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 5 ተከሳሾች ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት እንዲነሱ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ዳኛው “ከችሎት ይነሱ አይነሱ” የሚለውን ለመበየን ለታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓም ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በእነ ክንዱ ዱቤ ደነቀው መዝገብ የተከሰሱ 5 ተከሳሾች ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል።
አቶ ደበበ ሞገስ፣ አቶ ዘርዓይ አዝመራው ጎለንታው፣ አቶ ገብረስላሴ ደሴ አሰግድ፣ መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረ እና አቶ ሀብታሙ እንየው ፈረደ በጻፉት አቤቱታ “ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ አምሓራዊ ማንነታችንን መሠረት አድርጎ የሽብር ክስ በ06/10/2009 ዓ.ም. አቅርቦብን እየተከታተልን ቢሆንም፣ “ ክሳችንን በዚህ 2010 ዓ.ም በግራ ዳኛነት ተሰይመው በማየት ላይ የሚገኙት ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ጉዳያችንን በገለልተኝነት ወይም ገለልተኛ በመምሰል አይተው ፍትህ ይሰጡናል ብለን ስለማናምን እንዲነሱልን እናመለክታለን ብለዋል።
ተከሳሾች ዳኛው ጉዳያቸውን በገለልተኝነት ለማዬት ለምን እንደማይችሉ ዝርዝረው አቅርበዋል። ግለሰቡ እነሱ በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ አቋማቸውን ጽፈው ማውጣታቸው፣ ማንነታቸውን በመመካት ምንም አትፈጥሩም በማለት በችሎት ላይ እያሸማቀቁዋቸው መሆኑን እንዲሁም በእስር ቤት የሚፈጸምባቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳያቀርቡ ማገዳቸውን ዳኛው እንዲነሱላቸው በምክንያትነት ከጠቀሱዋቸው መካከል ይገኙበታል።

No comments:

Post a Comment