Saturday, November 11, 2017

አጭር መልዕክት ለብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ባልደረቦች በሙሉ! (ዶክተር ታደሰ ብሩ)

የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ሥራቸውና ስማቸው ለየቅል ከሆኑባቸው ተቋማት አንዱ ነው። ይህ ተቋም እንደ ስሙ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ ለብሄራዊ ደህንነት የሚጠቅሙ መረጃዎችን የሚሰበስብ በሆነ ነበር፤ ግን አልሆነም።
አሁን ባለሁ ሀቅ መሠረት የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት፣ ህወሓትን የሚቃወሙ ዜጎችን ሁሉ በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት “ህጋዊ ፈቃድ” የተሰጠው ተቋም ነው። የዚህ ተቋም አባላት በአገር ደህንነት ስም የዜጎችን የግል መኖሪያ ቤት፣ ቢሮ፣ የስልክና የኢሜል ግኑኝነቶች ይበረብራሉ። “የዓይኖቻቸው ቀለም” ያላማሩዋቸውን“ ዜጎች ያዋክባሉ፣ ይገርፋሉ፣ ያሳድዳሉ፣ ይገላሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው የሀገር ሀብት የህወሓት ሽማምንትን ደህንነት ለመጠበቅ ያባክናሉ። ውሎና አዳራቸው ዜጎችን ማሳደድ ነው። ከዚህም አልፎ ሕዝብ ከሕዝብ፤ የአንድ እምነት ተከታዮች ከሌላ እምነት ተከታዮች ጋር የሚያጋጩ አሻጥሮችን ይሠራሉ። ዘወትር ወንጀሎችን እየሠሩ በሌሎች ላይ ይደፈድፋሉ። ፍርድ ቤቶች ፍርደገምል ውሳኔ እንዲሰጡ ያደርጋሉ። ... ብዙ እጅግ ብዙ ለዓይንና ጆሮ የሚቀፉ ተግባራትን ይፈጽማሉ።

ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራችን ተሸማቀን እንድንኖር፤ አሊያም አገር ለቀን እንድንሰደድ የሚያደርጉን የዚህ ተቋም ባልደረቦችና ተባባሪዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ የተቋሙ ባልደረቦች በሙሉ አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ እገነዘባለሁ። በሆነ ምክንያት ገብተው መውጣት ያልቻሉ፤ ከዛሬ ነገ እለቃለሁ እያሉ የሰነበቱ፤ አሊያም ”የእንጀራ ጉዳይ” ሆኖባቸው ባያምኑበትም የታዘዙትን በመፈፀም ላይ የሚገኙ ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ። እነዚህ ወገኖች በሚሠሯቸው ወንጀሎች መሸማቀቃቸው ለራሳቸውም ሆነ ስቃዩ ለሚደርስብን ወገኖች የሚፈይደው ነገር የለም። እነዚህ ወገኖች ይሰሙኛል ብዬ በማሰብ አንዳንድ ነገሮችን ላነሳ እፈልጋለሁ።
ሥራችሁን ሳትለቁ ለገዛ ራሳቸው ህሊና፤ ለልጆቻችሁ፣ ለሀገራችሁ እና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን መፈፀም ትችላላችሁ። ህወሓትን ከስልጣን በማስወገድ ሂደት አስተጽዖ በማድረግ የለውጡ አካል የመሆን እድል አላችሁ። የለውጡ እንቅፋት ብትሆኑ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መወገዳችሁ አይቀርም፤ ስማችሁና ክብራችሁ እንደጎደፈ ይኖርል። የለውጡ አካል ከሆናችሁ ግን ራሳችሁ ነፃ ታወጣላችሁ፤ ስማችሁና ክብራችሁን ታድሳላችሁ፤ የለውጡን መልካም ፍሬ ከሕዝብ ጋር ትቋደሳላችሁ። ይህንን ለማድረግ የአሁኑ ሥራችሁን መልቀቅ አያስፈልጋችሁም።
ሰብዓዊ ህሊና እና የሀገር ፍቅር ያላችሁ የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ባልደረቦች ጠላት ጉያ ውስጥ ሆናችሁ ጠላትን የማዳከም ከፍተኛ አቅም አላችሁ። የህወሓት የስለላ ድርጅት ውስጥ ሆናችሁ ራሱ ህወሓትን ሰልሉት፤ ደካማና ጠንካራ ጎኖቹን አጥኑ፤ ያገኛችሁትን መረጃ ደግሞ ሥርዓቱን ለሚቃወሙ ኃይሎች አካፍሉ። ክፉ ሥርዓት ልብ ውስጥ መሆናችሁ፤ ከማንም በላይ ይህን ክፋት ለማስወገድ በተመቸ ቦታ ላይ ያላችሁ መሆናችሁን ተገንዘቡ ! እጃችሁ ውስጥ ያለውን ኃይል ረብ ላለው ነገር አውሉት፤ እድሜ ልካችሁን የምትኮሩበት ታሪክ ትፈጽማላችሁ። ልጆቻችሁና ወገኖቻችሁ በእናንተ ይኮራሉ።
ህወሓት እንዲህ በተዋከበትና በተዳከመበት ወቅት የራሳችሁን እና የቤተሰቦቻችሁን ታሪክ የማደስ እድል አታስመልጡ።

No comments:

Post a Comment