Friday, November 24, 2017

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ም/ል ፕሬዚዳንት ሊጠፉ ሲሉ ተያዙ

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ምስጋናው አድማሱ አንድ የደህንነት ሰው አስከትለው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሊሰወሩ ሲሉ በደህንነት ሃይሎች ህዳር 13 ቀን 2010 ዓም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ቀደም ብለው በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ምስጋናው አድማሱ በአሁኑ ሰአት በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
የጉሙዝ ተወላጅ የሆኑት ም/ል ፕሬዚዳንቱ፣ እርሳቸው ዋና ፕሬዚዳንት ሆነው ለመሾም ተስፋ አድርገው በነበረበት ሰአት፣ ከእርሳቸው ስር የነበሩት የበርታው ተወላጅ አቶ አሻድሊ ሃሰን ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመሾማቸው ሲበሳጩ ቆይተዋል ።
በክልሉ የስልጣን ድልድል መሰረት የፓርቲው ሊቀመንበር ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲሆን፣ አዲሱ ተሿሚ ፕሬዚዳንት የፓርቲውንም የሊቀመንበርነት ቦታ ለመያዝ አጀንዳ ማቅረቡ ለሁለቱ የክልሉ ባላስልጣናት ጸበ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ውዝግብ ውስጥ እያሉ የቦሎጂጋንፎይ ግጭት የተነሳ ሲሆን ፣ ለግጭቱ መነሳት ዋናው ፕሬዚዳንት ምክትል ፕሬዚዳንቱን ተጠያቄ አድርገዋል። ም/ል ፕሬዚዳንቱ ሆን ብሎ ቀስቅሶታል በተባለው ግጭት 9 የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል።
አቶ ምስጋናው ለአዲሱ ፕሬዚዳንት አልታዘዝም በማለታቸው ጉዳዩ በፌደራል መንግስቱ እንዲታይና እርሳቸውም ወደ ፌደራል ተዛውረው እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ የፌደራል ባለስልጣናት ግን ጥያቄያቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም።
አቶ ምስጋናው እርሳቸውም እንደ ቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ያረጋል አይሸሹም እታሰራለሁ የሚል ፍርሃት አድሮባቸው እንደነበርና በዚህም ፍርሃት የተነሳ ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
አምባሳደር ምስጋናው አንድ የጉሙዝ ተወላጅ በማን እንደተደበደበ ሳይታወቅ ተደብድቧል በማለት የወረዳው አስተዳዳሪን በማዘዝ በአማራ ተወላጆች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጋቸውን የገለጹት ምንጮች፣ የፖለቲካ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የወሰዱት እርምጃ በፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እንደታወቀባቸው እና የዋናውን ፕሬዚዳንት ስልጣን አልቀበልም ቢሉ እንደ ቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ያረጋል አይሸሹም እታሰራለሁ የሚል ፍርሃት ስላደረባቸው ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸውን ምንጮች አስረድተዋል።
ከወር በፊት ለቀን ሰራተኝነት ከኦሮምያ ክልል ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቡ የኦሮሞ ተወላጆች በአንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ተደርጎ በመኪና ተጭነው ከዳቡስ ወንዝ ማዶ መጣላቸውንና ወደ ክልሉ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በክልሉ የህወሃት ቢዝነስ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ ለእነሱ የመከላከያ ሰራዊት ልዩ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።
x

No comments:

Post a Comment