Tuesday, November 28, 2017

በትምህርት ጥራት ዙሪያ መምህራኑና ባለስልጣናቱ አልተግባቡም

በደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ-ጂንካ ‹‹የአንጋፋና ጡረተኛ መምህራን የሜዳሊያ መስጠት›› ፕሮግራም ላይ በትምህርት ጥራት ዙሪያ በተደረገ ውይይት በደቡብ ክልል በአጠቃላይ ፣በተለይ ደግሞ በደቡብ ኦሞ ዞን የትምህርት ጥራት ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የክልሉ መምህራን ማኅበር ተወካይና የዞኑ መምህራን ገልጸዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ ይህንን የባለሙያዎቹን አስተያየት ሊቀበሉ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ህዳር9 ቀን 2010 ዓም በተካሄደው ስነስርዓት የክልሉን መምህራን-ማኅበር በመወከል የተገኙት መምህርት ጤናዬ ታደሰ የትምህርት ጥራቱ--“ከትምህርት ፖሊሲውና የትምህርት መዋቅሩ በመነጩ ችግሮች በአሁኑ ጊዜ ትናንት ‘የማያነቡ ተማሪዎች’ እያልን ከምንገልጽበት አደጋ ተሻግሮ ዛሬ ‹የማያነቡ› መምህራን ማፍራት ደረጃ-ተሸጋሯል” ብለዋል። “ ይህ ችግር ሥር እየሰደደ በመሆኑ እንደአገርም እንደክልላችንም አስደንጋጭና በእጅጉ አሳሳቢ ስለሆነ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተበጀለት በአጠቃላይ የአገራችን ዕድገትና ልማት ቁልፍ በሆነው የሰብዓዊ ሃብት ልማት ላይ የሚያስከትለው አደጋ አገሪቱን በአጭር ጊዜ የከፋ አዘቅት ውስጥ ይከታታል፡፡›› በማለት የማኅበራቸውን ግምገማ ውጤት አስረድተዋል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዓለማዬሁ ባውዴ የወ/ሮ ጤናዬን ሃሳብ በመቃወም ‹‹የመንግሥታችን የትምህርት ፖሊሲ-የአገራችን ትምህርት ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማድረስና ተማሪዎቻችንን በዓለም ተወዳዳሪ ለማድረግ ነው፡፡ ችግሩ የፖሊሲ አይደለም፣የአፈጻጸም ነው-ችግሩ የሁሉም ባለድርሻዎች ነው፡፡››በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል፡፡
መምህራን በበኩላቸው “ችግሩ የቤተሰብ፣ የተማሪም ሆነ የመምህሩ አይደለም፣ የመንግስት የትምህርት ፖሊሲና መዋቅር ነው›› በማለት የአስተዳዳሪውን አስተያየት አጣጥለውታል፡፡
መምህራኑ በትምህርት ሽፋን ስም ትምህርትን እንደጸበል በማዳረስ የማያነቡ ተማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ ከሆነና 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ የወደቁ ተማሪዎችን 7ኛ እና 8ኛ ክፍል እንዲያስተምሩ በማድረግ የትምህርት ጥራቱን ማሻሻል አይቻልም ብለዋል፡ ትምህርትን እንደሸቀጥ የሚያቀርበው- በማያነቡ መምህራን የሚያስተምረው--ትውልድ ገዳይ ፖሊሲን መሸፈንም ሆነ መከላከል በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል›› በማለት መምህራን አክለው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚህ ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን ‹የተከፈተው› ጂንካ ዩኒቨርስቲ እስከዛሬ ትምህርትና የተማሪዎች አገልግሎት ባለመጀመሩ በዩኒቨርስቲው የተመደቡ ተማሪዎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ አቅም የፈቀደላቸው ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ሲሆን ሌሎች ግን በከተማዋ ነዋሪዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ዩኒቨርስቲው ድረስ በአካል ተገኝቶ የተመለከተው ተባባሪ ዘጋቢያችን ገልጿል።

No comments:

Post a Comment