Thursday, November 2, 2017

ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቀውን ሕገ ውሳኔ የአሜሪካ ምክር ቤት በአስቸኳይ እንዲያጸድቅ የኮሎራዶ ተወካይ የሆኑት ማይክ ኮፍማን ጠየቁ።

ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቀውን ሕገ ውሳኔ የአሜሪካ ምክር ቤት በአስቸኳይ እንዲያጸድቅ የኮሎራዶ ተወካይ የሆኑት ማይክ ኮፍማን ጠየቁ። ማይክ ኮፍማን ትላንት በምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱ ሕገ ውሳኔውን እስካሁን ማዘግየቱ እጅግ ያሳዘናቸው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። በኮሎራዶ የ6ኛው የምርጫ ክልል ተወካይ የሆኑትና ከኢትዮጵያውያን ጋር በሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ በቅርብ በመስራት የሚታወቁት ማይክ ኮፍማን ትላንት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱ ሕገ ውሳኔውን እስካሁን ማዘግየቱ እጅግ ያሳዘናቸው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። አሜሪካ ህገ ውሳኔውን በማሳለፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ተባባሪ መሆን ትችላለች ብለዋል። ተወካዩ አክለውም አሜሪካ ያሏትን ተቋማት በመጠቀም በኢትዮጵያ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ማገዝ ትችላለች።ውሳኔውን ማጽደቅ አስፈላጊ የሚሆነውም ለዚህ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ አሉ ማይክ ኮፍማን በሀገሪቱ እየተጠየቀ ያለውን ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሎቢስቶችን ወይንም ጎትጓቾችን በመቅጠር የምክር ቤት አባላት ስለ ሀገሪቱ መልካም አመለካከት እንዲኖራቸው የሕዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት ላይ ተጠምዷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ይህን ከማድረግ ይልቅ በሀገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዲሞክራሲ እጦት ችግሮችን መፍትሄ ቢሰጥ ይሻል ነበር ብለዋል። ይህን ቢያደርግ ነው በአሜሪካ ምክር ቤት ያሉ አባላት በኢትዮጵያ ስላለው መንግስት መልካም አመለካከት የሚኖራቸው ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ለሁለት ጊዜያት ሕጉ ለውሳኔ እንዲቀርብ ቀጠሮ ከተያዘለት በኋላ ላልታወቀ ጊዜ መተላለፉ እንዳበሳጫቸው ተናግረዋል። ይህም የሆነው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ሕጉ የሚጸድቅ ከሆነ ከአሜሪካ ጋር በጸጥታ ጉዳዮች ላይ አልተባበርም በማለቱ እንደሆነ መረዳት ችያለሁ ሲሉ ገልጸዋል። አገዛዙም በገዛ ሕዝቦቹ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ቀጥሎበታል ብለዋል። አሁን ይህ ምክር ቤት ማድረግ ያለበት ሕገ ውሳኔውን አጽድቆ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ መርዳት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ኤች አር 128 የተባለው ሕገ ውሳኔ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ሁሉን አቀፍ መንግስት እንዲቋቋም፣በሀገሪቱ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ግድያ የፈጸሙ የጸጥታ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡና በገለልተኛ አለም አቀፍ አካላት ምርመራ እንዲካሄድ ይጠይቃል። ሕጉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ግድያና ሰቆቃ እንዲሁም የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ግለሰቦች ላይ የአሜሪካ መንግስት ማእቀብ እንዲጥል ይደነግጋል።

No comments:

Post a Comment