Friday, November 24, 2017

የኦሮሚያ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮ ሜቴክ ከክልሉ የድንጋይ ከሰል በማውጣትና በመሸጥ ሲያከናውን የነበረውን ህገወጥ ድርጊት ማስቆሙን አስታወቀ

የኦሮሚያ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮ ሜቴክ ከክልሉ የድንጋይ ከሰል በማውጣትና በመሸጥ ሲያከናውን የነበረውን ህገወጥ ድርጊት ማስቆሙን አስታወቀ። ቢሮው “ህገ ወጥ የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር በድብቅ ቢፈጸምም ከብዙሃኑ ህዝብ እይታ ግን ፈጽሞ ሊሰወር አይችልም” በሚል ባወጣው መግለጫ ሜቴክን ብቻ ሳይሆን የክልሉን ሃብት በመዝረፍ የተሰማሩ አካላት ላይ የምወስደውን ርምጃ እቀጥላለሁ ብሏል። የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/በሕግ ከተቋቋመበትና ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ከኦሮሚያ የድንጋይ ከሰል በማውጣት እየሸጠ ነው ሲሉ በፓርላማ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንደገመገሙት ሰሞኑን መዘገባችን ይታወሳል። በምክረ ሃሳብ ነው የድንጋይ ከሰሉን ከክልሉ ማውጣት የጀመርኩት ያለው ሜቴክ ይህንን ምክረ ሃሳብ ያቀበሉት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚመክሯቸውና የሚያማክሯቸው ዶክተር አርከበ እቁባይ መሆናቸውን ገልጿል። ሜቴክ እየሰራው ያለው ስራ ህብረተሰቡን እያስቆጣ ነው በሚል ቋሚ ኮሚቴው ላነሳው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ላልፈለገው ሜቴክ ዛሬ ላይ ክልሉ ራሱ ንብረቴን መዝረፍ አትችልም ሲል ምላሽ ሰጥቶታል። ህገ-ወጥ የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር በድብቅ ቢፈጸምም፣ ከብዙሀኑ ህዝብ እይታ ግን ፈጽሞ ሊሰወር አይችልም በሚል የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ ባወጣው መግለጫው አስታውቆታል።
ለሜቴክ ብቻ ሳይሆን በክልሉ በህገወጥ መንገድ የማዕድን ሀብትን በመዝረፍ፣በመሸጥና በማስተላለፍ ላይ የተሰማሩ ልማታዊ ያልሆኑ ባለሃብቶችም ሆነ ግለሰቦች ላይ የምወስደውን ርምጃ አጠናክሬ እቀጥላሉ ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫውን አውጥቷል። አቶ አርከበ ናቸው የመከሩኝ ሲል የቆየው ሜቴክ አሁን ደግሞ ከ2004 ጀምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአቴ የሚሆን የድንጋይ ከሰል ማዕድንን በአጨቦና ወተቴ አካባቢ እንዳመርት የማዕድን ሚኒስቴር ፍቃድ ሰጥቶኛል ሲል አንድ ገጽ ደብዳቤ በማሳያነት አቅርቧል። ተሰጠኝ የሚለው ደብዳቤ ግን ግልጽነት የጎደለወ፣የመንግስት ግብር ህጋዊ በሆነ መልኩ መክፈሉን የማያሳይ በቂ ሰነድ የሌለበት፣ምንም አይነት የስምምነት ሰንድና ሌሎች ህጋዊ ሂደቶችን መከተሉንም አያመለክትም ተብሏል። ክልሉ ግን ሜቴክ አለኝ ያለውን ደብዳቤ ወደ ጎን በመተው ሜቴክ የከሰል ድንጋይ ማዕድን ምርቱን ምንም አይነት ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው ወደ ሌላ ቦታ ሲያዘዋውር መቆየቱን ደርሰንበታል ነው ያለው።ይህንን ያጋለጠው ደግሞ የንብረቱ ባለቤት የሆነው ህዝብ ነው ሲል ምላሹን ሰጥቷል። ስለዚህም የዚህ ሃብት ባለቤት የሆነውን ህዝብ ይዘንና በሕገመንግስቱ የተሰጠንን የተፈጥሮ ሀብታችንን የማስተዳደር መብት ተጠቅመን ይህን ድርጊት አስቁመናል፥ ጉዳዩንም በማጣራት ላይ እንገኛለን ብሏል የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ ባወጣው መግለጫው። በሌሎች ሲመዘበር የቆየውንም ሀብት በመከላከል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረጉን ስራም አቀጥልበታለሁ ብሏል ክልሉ። ለዚህ ደግሞ ማንኛውም የሚመለከተው አካል ከህብረተሰቡ ጎን በመቆም አላግባብ የህብረተቡን ንብረት የመመዝበር ድርጊት እንዲታገል የኦሮሚያ የውሃ ሃብት ቢሮ ጥሪውን አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment