Friday, November 24, 2017

የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱላቸው ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ጠየቁ

በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት አምስቱ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ኮሚቴ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ፣ አቶ ጌታቸው አደመ ሰረጸ፣ አቶ አታላይ ዛፌ ገ/ማሪያም፣ አቶ አለነ ሻማ በላይ እና አቶ ነጋ ባንተይሁን በራ የ4ኛ ችሎት የግራ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት እንዲነሳ አቤቱታቸውን በፅሁፍ አስገብተዋል።
ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት በወልቃይት የአማራ ማንነት ላይ ግልጽ የሆነ ፖለቲካዊ አቋም ይዘው በሆርን አፍሪካ አፌር አማርኛ ድረገጽ ላይ አቋማቸውን አሳውቀዋል። ግለሰቡ የገዥው ፓርቲ ህወሃት አባልና የሆኑና በአመለካከታቸውም በሽብር ክስ ስም ከከሰሳቸው አቃቤ ሕግ የተለዩ ባለመሆናቸው ከእሳቸው ፍትሕ እንደማይጠብቁና ዳኛው ይቀየሩላቸው ዘንድ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ በዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ላይ ተከሳሾች ችሎት ላይ አሰምተውት የነበረውን ተቃውሞ በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ባዘዘው መሰረት በዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት የተጻፈውን 46 ገጽ ጽሁፍ አባሪ በማድረግ ከማመልከቻቸው ጋር ለፍርድ ቤቱ አስገብተዋል።

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 27 ቁጥር 1(ሠ) ላይ በተዘረዘረው ዝርዝር ሕግ መሰረት በሚዲያ አቋም ይዞ እየፃፈና እየተናገረ ከወልቃይት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተከስነው ላይ ዳኛ ሆኖ መሰየም አይገባውም። ስለዚህም የዳኛው ወገንተኝነት እየታወቀ ከሕግ አግባብ ውጪ ጉዳያችንን ሊያይ አይችልም ሲሉ የሕግ አንቀጾችን በመጥቀስ ዳኛው እንዲነሳላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ገጽ 14 ላይ 3ኛ አንቀጽ ስለ ብሄር ማንነት ዕውቅና በተነተኑበት ጽሁፋቸው ላይ ''ስለሆነም እውቅና ይሰጠው የተባለ ማንነት በአገሪቱ በየትኛውም ክፍል በሚገኝ መልክ ዓምድር ውስጥ የሰፈረ ማኅበረሰብ እውቅና የተሰጠው ከሆነ ይህ እውቅና ያገኘው የብሄር ማኅበረሰብ ከሰፈረው መልክዓ ምድር ውጪ የሚገኝ ማንኛውም ማኅበረሰብ ይህንኑ እውቅና እንዳገኝ ይሰጠኝ ብሎ የሚያቀርበው የማንነት ጥያቄ ሊኖር አይችልም።'' ሲሉ አቋማቸውን በግልጽ አሳውቀዋል።
ግለሰቡ በገሃድ በሚታይ መልኩ በዚሁ ጽሁፋቸው በገጽ 15 አንቀጽ 2 ላይ ''የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ሊያሰጠው የሚችል ልዩ ማንነት የለውም።'' ብለዋል። በተጨማሪም በገጽ 19 3ኛ አንቀጽ ላይ ደግሞ ''የወልቃይት ሕዥብ ከሽግግር መንግስቱ ወቅት ጀምሮ ለግማሽ ክፍለዘመን በትግራይ ክልል ውስጥ የቆየ ስለሆነ በሕገመንግስቱም ሆነ በትግራይ ክልል ሕግ መሰረት የአማራ ማንነት መጠየቅ አይችሉም።'' ሲሉ የህወሃት አባልና ደጋፊ መሆናቸውን በዓደባባይ በጽሁፋቸውን በማሳወቃቸው ግለሰቡ በሕግም ሆነ በሞራል የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላትን ለመዳኘት መሰየም አይገባቸውም በማለት ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤያቸውን በመግለጽ ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲነሱላቸው ጠይቀዋል።
x

No comments:

Post a Comment