Thursday, November 2, 2017

የሕወሀትን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ የኢትዮጵያ ሰራተኞች በጋራ እንዲቆሙ በስደት የሚገኙ የቀድሞ ማህበራት መሪዎች ጥሪ አቀረቡ

የሕወሀትን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ የኢትዮጵያ ሰራተኞች በጋራ እንዲቆሙ በስደት የሚገኙ የቀድሞ ማህበራት መሪዎች ጥሪ አቀረቡ። በአሁኑ ጊዜ ያለው ትልቁ አጀንዳ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማዳን እንጂ በሰራተኛ ሕጉ ላይ አንቀጾችን የማስተካከል ጉዳይ እንዳልሆነ የቀድሞ የሰራተኛ መሪዎች ባወጡት መግለጫ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በቅርቡ የሰራተኞች መብትን የሚመለከተውን አዋጅ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ ለመጥራት ማቀዱን መግለጹ ይታወሳል። የቀድሞው የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች አዲሱን የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የባርነት አዋጅ ነው ብለውታል። በስደት ላይ የሚገኙት የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች ባወጡት መግለጫ እንዳሉት በኢትዮጵያ በሰራተኞች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሁኔታዎች በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ባለመኖሩ መላው ህዝብ በግፍ አገዛዝ እየተበደለ መሆኑን በመግለጫቸው አመልክተዋል። በቀድሞው ኮንፌዴሬሽን ከነበሩት 9 ፌዴሬሽኖች የአንደኛውና የንግድ የቴክኒክና ሕትመት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት እቶ ሐይሉ ኡርጌሳ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የሰራተኛው መብት ሙሉ በሙሉ ሊከበር የሚችለው በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው። እናም አበራ ገሙን በመሰሉ የቀድሞ አንጋፋ መሪዎች መስዋዕትነት የተከበሩ መሰረታዊ የሰራተኛ መብቶች በሕወሃት የግፍ አገዛዝ እየተናዱ መምጣታቸውን ነው የገለጹት። የሰራተኛ መብቶች እንዲደፈቁ ምክንያት የሆነው ደግሞ ነጻ ፍርድ ቤትና ነጻ ማህበር ባለመኖሩ መሆኑን መግለጫው ያሳስባል።እንደ ቀድሞዎቹ የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች መግለጫ በኢትዮጵያ ላለው የግፍ አገዛዝና የሰራተኞች ችግሮች ዋነኛው ምንጭ ሕወሃትና ህወሃት ብቻ ነው። ስለሆነም ይላል መግለጫው በአሁኑ ጊዜ መላው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ሊያደርጉት የሚገባው ሕዝቡ እያካሄደ ያለውን የሞት ሽረት ትግል መደገፍ ነው ብሏል። በስደት የሚኖሩት የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች ለኢሳት በላኩት መግለጫ እንዳሉት የህወሃትን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ የኢትዮጵያ ሰራተኞች በጋራ ሊቆሙ ይገባል። በአሁኑ ጊዜ ያለው ትልቁ አጀንዳ ኢትዮጵያን አንደ ሀገር ማዳን እንጂ በሰራተኛ ህጉ ላይ አንቀጽ የማስተካከል ጉዳይ እንዳልሆነም ነው የገለጹት ። አሁን ያሉት የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን መሪዎች ከሕወሃት ጋር ባላቸው ግንኙነት የሰራተኛውን ጥቅም በማስከበር ዘለቄታዊና ሀገራዊ ራዕይ ይዘው ከዳር ያደርሱታል ተብሎ እንደማይታመንም በስደት የሚኖሩት የቀድሞ ሰራተኛ ማህበራት መሪዎች በመግለጫቸው አመልክተዋል።

No comments:

Post a Comment