Thursday, November 16, 2017

ለውጥ የሚጠይቁ የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ቁጥር እየጨመረ ነው

ከመከላከያ ሰራዊት የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በመከላከያ ውስጥም ሆነ አጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ የሚጠይቁ የመከላከያ አዛዦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በቅርቡ በተካሄዱ የመከላከያ ግምገማዎች ላይ በርካታ መኮንኖች አገዛዙ የሚከተለው ፖሊሲ አገሪቱን አደጋ ውስጥ የሚጥልና ግጭቶችንም የሚያበብስ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ሊመጣ ይገባዋል ብለዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱት ተቃውሞዎች ወታደሮች ግራ መጋባታቸውን የገለጹት አዛዦች፣ ህዝባዊ ድጋፍ አለኝ የሚል መንግስት እንዴት ይህን ያክል ተቃውሞ ሊገጥመው ቻለ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል። የመከላከያው ሚና ምን መሆን አለበት የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል። መከላከያው ድንበር መጠበቁን ትቶ በየጎጡ መሰማራቱ ከአገራዊ ተልእኮው ጋር የሚጋጭ
መሆኑንና ከህዝቡ ጋር በሚያደርጉት ውይይት የመከላከያ አባላት ልባቸው እየተከፈለ አብዛኛውን ጊዜ ደጋፊ እየሆኑ መምጣታቸውንም አዛዦች በውይይታቸው አንስተዋል። ተቃውሞዎች እየተጠናከሩ የሚሄዱ ከሆነ የመከላከያ ሰራዊቱን አዞ ሰላም እና መረጋጋት ለማስከበር እንደከብድ በመግለጽ፣ አሁን የሚታየው አለመረጋጋት ይበልጥ ከመክፋቱ በፊት ፖለቲካዊ መፍትሄ በአፋጣኝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከብሄር ጋር በተያያዘ የሚሰማቸው ስሜትም ሌላው የውይይት አጀንዳ ነበር። የኦሮሞ፣ አማራና የደቡብ የመከላከያ አባላት በአማራ እና በኦሮምያ ላይ የሚወሰዱትን እርምጃዎች የመቃወም አዝማሚያ እያሳዩ መምጣታቸውም በውይይቱ ላይ የተነሳ ሲሆን፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተወለዱበት ክልል እንዳይመደቡም ሀሳብ ቀርቧል።
ከዚህ ቀደም ባልታዬ ሁኔታ የመከላከያ መኮንኖች በአገሪቱ ፖለቲካ ዙሪያ ጠንካራ ውይይት ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል። አገሪቱ ወደ አልሆነ አቅጣጫ እያመራች መሆኑን አብዛኞቹ የመከላከያ አባላት እያመኑበት መጥተዋል።
በመከላከያ ውስጥ ለውጥ ሊኖር ይገባል የሚለውም ሃሳብ ዋና የውይይት አጀንዳ ነበር። በተለይ እድሜያቸው የገፉ እንደ ጄ/ል ሳሞራ የኑስና ሌሎች ነባር የህወሃት ታጋዮች በጡረታ እንዲገለሉና የስልጣን ክፍፍሉ ወታደራዊ መርህን እንጅ ብሄርን ማእከል ያደረገ እንዳይሆን ሃሳብ ያቀረቡ አዛዦችም ነበሩ። የመከላከያው አወቃቀር ከብሄር ይልቅ ችሎታንና ስራን ማእከል ያደረገ ካልሆነ መከላከያው ጥንካሬውን እንደጠበቀ ለማስኬድ እንደማይቻል አዛዦች ገልጸዋል።
አንዳንድ ጊዜ ያልጠበቁዋቸው ጥያቄዎች የገጠሙዋቸው አወያዮቹ፣ በመከላከያ ውስጥ ስለሚኖረው ለውጥ የፖለቲካዊ አመራሩ ውሳኔ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ጥልቅ ተሃድሶው የተፈለገውን ውጤት አለማምጣቱ አገሪቱ አሁን ለገባችበት ችግር ዋና ምክንያት መሆኑንም አወያዮች ገልጸዋል። መከላከያው የአገሪቱን ደህንነት ከውጭም ከውስጥም መጠበቅ ግዴታው መሆኑን በመጥቀስ፣ በውስጥ የተፈጠረው ችግር በሻዕቢያና በግብጽ አቀናባሪነት የተፈጸመ በመሆኑ፣ መከላከያው የውስጥ ችግር ለማስጠበቅ መሰማራቱ ተገቢ መሆኑንም አወያዮቹ ገልጸዋል። ይህኛውን ምክንያት ተወያዮች አልተቀበሉትም። በኢትዮ ሶማሊ ክልል የደረሰው መፈናቀል እንዴት በሻዕቢያና ግብጽ የተደረገ ነው ሊባል ይችላል፣ ጠ/ሚኒስትሩ ራሳቸው እኮ በአካባቢው ባለስልጣናት ትእዛዝ የተፈጸመ ነው ብለው ተናግረዋል የሚል ሃሳብ ቀርቦ ክርክር ተካሂዶበታል።
ከመኮንኖች ውይይት በሁዋላ ሌሎች የመከላከያ አባላትን ለማወያየት እቅድ ተይዟል።
x

No comments:

Post a Comment