Wednesday, September 27, 2017

በነገሌ ቦረና አካባቢ ውጥረት መስፈኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

(ኢሳት ዜና መስከረም 17 ቀን 2010 ዓም) በነገሌ ቦረና አካባቢ ውጥረት መስፈኑን ነዋሪዎች ተናገሩ
በኦሮምያ ክልል በነገሌ ቦረና ትናንት ወረቀት መበተኑን ተገልጾ ውጥረት መስፈኑ ታውቋል። ወረቀቱን የሶማሊ ልዩ ሃይል ጦር እንደበተነው ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ወረቀቱ “ ነገሌ ቦረና የሶማሊ ክልል መሬት በመሆኑ፣ ማንኛውም የኦሮሞ ተወላጅ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ” የሚል ይዘት ያለው መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ይህንን ተከትሎ ከትናንትና ጀምሮ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት እንደሚታይ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የአቶ አብዲ ሙሃመድ እንደሆነ በሚታመነው የፌስ ቡክ ገጽ ላይ፣ ፕሬዚዳንቱ ኢሳት፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትን እንዲሁም የቀድሞውን የህወሃት ታጋይና ኢታማጆር ሹም የሆኑትን ጄ/ል ጻድቃን ገብረትንሳኤን በእርሳቸው ላይ እንደተነሱባቸው አድርገው ተችተዋል። ኢሳትና ግንቦት7 ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር አንድ ሆነው በእርሳቸውና በክልላቸው ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን ገልጸዋል። “አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እኔን ከስልጣን የማውረድ ስልጣን የለውም፣ እንዴው በመጪው ምርጫ እወዳደራለሁ” በማለት፣ ጄ/ል ጻድቃን አቶ ሃይለማርያም በእርሳቸው ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ምክር የለገሱ መሆናቸውን በመጥቀስ ፕሬዚዳንቱ ጽፈዋል።
ምንም እንኳ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ችግሩን ለመፍታት መስማማታቸው በመገናኛ ብዙሃን ቢገለጽም፣ የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት አልፎ አልፎ ጥቃት እየፈጸሙ መሆናቸውን ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በሁለቱ ክልሎች ድንበር ላይ ተነስቶ በነበረው ግጭት ከ55 ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተገድለዋል። ከ1 ሺ በላይ ዜጎች በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ነው። አሁንም ድረስ ከክልሉ የሚፈናቀሉ ዜጎች አሉ። የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ተፈናቃዮችን በትውልድ ቦታቸውን እየወሰዱ ማስፈራቸው፣ ዜጎቹን ወደ ሶማሊ ክልል መመለስ እንደማይቻል በማወቃቸው ሊሆን እንደሚችል ወኪላችን ገልጿል።
መከላከያ ሰራዊት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከሁለት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። በእነዚህ አካባቢዎች መከላከያ ለምን እንዳልተመደበ ግን የተናገሩት ነገር የለም።
አቶ አብዲ ሙሃመድ በምስራቅ እዝ አዛዦችና በጄ/ል ሳሞራ የኑስ በኩል ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው።

No comments:

Post a Comment