Wednesday, September 20, 2017

በደቡብና ኦሮምያ ድንበር አካባቢ በተነሳው ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ45 በላይ ደረሰ

(ኢሳት ዜና መስከረም 10 ቀን 2010 ዓም) በደቡብና ኦሮምያ ድንበር አካባቢ በተነሳው ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ45 በላይ ደረሰ
ኢሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ተወላጆች እንደገለጹት በአማሮ ወረዳ አካባቢ ከሃምሌ 16 ቀን ጀምሮ በተነሳው ግጭት እስካሁን በተጠናከረው መረጃ 46 ሰዎች ሲገደሉ ከ50 በላይ ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል ተኝተዋል። 2 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ፣ ከ1500 ያላነሱ ቤቶች ተቃጥለዋል ወደ 100 ሺ የሚጠጉ ዜጎች ተፈናቅለው ተራራ ላይ ለመስፈር ተገዷል። 
በጉጂ በኩል 25 ሰዎች፣ በኮሬ 17 እንዲሁም በቡርጂ በኩል 4 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አሃዙ በቡሌ ሆራ የተገደሉትን 6 ሰዎች አያካትትም።
በአሁኑ ሰአት አካባቢውን የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች ተቆጣጥረውት እንደሚገኙና በመጠኑም ቢሆን ግጭቱ መቀነሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ተፈናቃዮች ምንም አይነት እገዛ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል። ተራራ ላይ የወለዱ እናቶች መኖራቸውንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ከአማሮ ወደ ዲላ የሚወስደው መንገድ ዝግ እንደሆነ መብራትም ግጭቱ ከተነሳ ጀምሮ መቋረጡን ነዋሪዎች ገልጸዋል።


ግጭቱ እንደተነሳ በአካባቢው የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ አዛዥ ሻምበል ክፍሌ መገደሉንና ሌለ የፌደራል አባልም በከባድ ሁኔታ ቆስሎ ሆስፒታል መግባቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ግጭቱ የሁለቱን ክልሎች ለማካለል በሚል እንቅስቃሴ በተነሳ ማግስት የተጀመረ ነው። የሁለቱም ክልል ባለስልጣናት ወደ አካባቢው መንቀሳቀሳቸውንና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን፣ በዚህም የተነሳ ግጭት መነሳቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የሚገርመው ደግሞ ይላሉ ነዋሪዎች፣ ህዝቡ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበትና በስቃይ ውስጥ እያለ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ ፣ ዛሬ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በሚል ማምጣቻውና ህዝቡ እንደተቃወመው ገልጸዋል። የሰገን ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዋንጫውን ይዞ ሲገባ፣ ህዝቡ ይበልጥ ተቆጥቶ እንደነበር፤ በተጠራውም ስብሰባ ላይ ባለመገኘትም ተቃውሞውን መግለጹን ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment